ዘዳግም 5:1-21

ዘዳግም 5:1-21 NASV

ሙሴ እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ እስራኤል ሆይ፤ በዛሬዋ ዕለት በጆሯችሁ የምነግራችሁን ሥርዐትና ሕግ ስሙ፤ አጥኗቸው፤ በጥንቃቄም ጠብቋቸው። አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ ከእኛ ጋራ ቃል ኪዳን ገብቷል። እግዚአብሔር ይህን ቃል ኪዳን የገባውም ከአባቶቻችን ጋራ ሳይሆን፣ ዛሬ እዚህ በሕይወት ከምንገኘው ከእኛ ከሁላችን ጋራ ነው። እግዚአብሔር እናንተን በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ፊት ለፊት አነጋገራችሁ። እናንተ ግን እሳቱን በመፍራት ወደ ተራራው ስላልወጣችሁ፣ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ለእናንተ እነግራችሁ ዘንድ እኔ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል ቆምሁ። እርሱም እንዲህ አለ፤ “ከግብጽ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም ከምድር በታች ወይም ውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ነገሮች በማናቸውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ፤ አትስገድላቸው ወይም አታምልካቸውም፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር፣ የሚጠሉኝን ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆቻቸውን የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። ለሚወድዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺሕ ትውልድ ፍቅርን የማሳይ ነኝ። የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አታንሣ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚያነሣውን በደል አልባ አያደርገውምና። አምላክህ እግዚአብሔር ባዘዘህ መሠረት የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ አክብረው። ስድስት ቀን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አከናውን። ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። በዚያ ቀን አንተም ሆንህ ወንድ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ በሬህ፣ አህያህ ወይም ማንኛውም እንስሳህ ወይም ደግሞ በደጅህ ያለ እንግዳ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ። ይህም አንተ እንዳረፍህ ሁሉ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ እንዲያርፉ ነው። በግብጽ ሳለህ አንተም ባሪያ እንደ ነበርህ፣ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ፤ ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ታከብረው ዘንድ አዘዘህ። አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝምና መልካም እንዲሆንልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ባዘዘህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር። አትግደል። አታመንዝር። አትስረቅ። በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ። በባልንጀራህ ቤትም ሆነ በመሬቱ፣ በወንድ ሆነ በሴት አገልጋዩ፣ በበሬውም ሆነ በአህያው ወይም የርሱ በሆነው በማንኛውም ነገር ላይ ዐይንህን አትጣል።”