አሁንም እስራኤል ሆይ፤ በሕይወት እንድትኖሩ፣ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ምድር እንድትገቡና እንድትወርሱ የማስተምራችሁን ሥርዐትና ሕግ ስሙ፤ ጠብቋቸውም። ባዘዝኋችሁ ላይ አትጨምሩ፤ ከርሱም አትቀንሱ፤ ነገር ግን የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ጠብቁ። እግዚአብሔር በበኣል ፌጎር ላይ ምን እንዳደረገ በዐይናችሁ አይታችኋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከመካከላችሁ በኣል ፌጎርን የተከተሉትን ሁሉ አጥፍቷቸዋል፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን የተከተላችሁት እናንተ ሁላችሁ ግን ይኸው እስከ ዛሬ በሕይወት አላችሁ። ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ። በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙና፣ “በእውነቱ ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው” ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና። በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ ቅርብ እንደ ሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው? ዛሬ እኔ በፊታችሁ እንዳስቀመጥሁት ሕግ ያለ ጽድቅ የሆነ ሥርዐትና ሕግ ያሉት ሌላ ታላቅ ሕዝብስ ማነው? ዐይኖቻችሁ ያዩአቸውን ነገሮች እንዳትረሱ፣ ደግሞም በሕይወት እስካላችሁ ድረስ ከልባችሁ እንዳይጠፉ ብቻ ተጠንቀቁ፣ ነቅታችሁም ራሳችሁን ጠብቁ። እነዚህን ለልጆቻችሁና ከእነርሱ በኋላ ለሚወለዱት ልጆቻቸው አስተምሯቸው። “በምድሪቱ በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ እኔን ማክበር እንዲማሩ፣ ለልጆቻቸውም እንዲያስተምሩ ቃሌን ይሰሙ ዘንድ ሕዝቡን በፊቴ ሰብስብ” ባለኝ ጊዜ፣ በኮሬብ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት የቆማችሁበትን ዕለት አስታውሱ። ተራራው በጥቍር ደመናና በድቅድቅ ጨለማ ተውጦ ሳለ ነበልባሉ ሰማይ እስከሚደርስ ድረስ በተቃጠለ ጊዜ መጥታችሁ ከተራራው ግርጌ ቆማችሁ። ከዚያም እግዚአብሔር በእሳቱ ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ፤ እናንተም የቃሉን ድምፅ ሰማችሁ፤ መልክ ግን አላያችሁም፤ ድምፅ ብቻ ነበርና። እርሱ ኪዳኑን ይኸውም እንድትከተሏቸው ያዘዛችሁን ዐሥርቱን ትእዛዛት ዐወጀላችሁ፤ ከዚያም በሁለት የድንጋይ ጽላት ላይ ጻፋቸው፤ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር ውስጥ የምትከተሏቸውን ሥርዐትና ሕግ እንዳስተምራችሁ በዚያ ጊዜ እግዚአብሔር አዘዘኝ።
ዘዳግም 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘዳግም 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘዳግም 4:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች