ዘዳግም 31:1-26

ዘዳግም 31:1-26 NASV

ከዚያም ሙሴ ወጥቶ እነዚህን ቃሎች ለእስራኤል ሁሉ ተናገረ፤ “እነሆ፤ መቶ ሃያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከእንግዲህ ልወጣና ልገባ አልችልም፤ እግዚአብሔርም ‘ዮርዳኖስን አትሻገርም’ ብሎኛል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ራሱ በፊትህ ቀድሞ ይሄዳል፤ እነዚህንም አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል፤ አንተም ምድራቸውን ትወርሳለህ፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው፣ ኢያሱም አንተን ቀድሞ ይሻገራል። እግዚአብሔር የአሞራውያንን ነገሥታት ሴዎንንና ዐግን ከነምድራቸው እንዳጠፋቸው፣ እነዚህንም ያጠፋቸዋል። እግዚአብሔር እነርሱን በፊታችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ያዘዝኋችሁን ሁሉ በእነርሱ ላይ ታደርጋላችሁ። ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።” ከዚያም ሙሴ ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው ሊሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ከዚህ ሕዝብ ጋራ ዐብረህ ስለምትገባ፣ ምድሪቱን ርስታቸው አድርገህ ስለምታከፋፍል በርታ፤ ደፋርም ሁን። እግዚአብሔር ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋራ ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ።” ሙሴም ይህን ሕግ ጽፎ፣ የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት ለሚሸከሙ ለሌዊ ልጆች፣ ለካህናቱና ለእስራኤል አለቆች ሁሉ ሰጠ። ከዚያም በኋላ ሙሴ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዕዳ በሚተውበት፣ የዳስ በዓልም በሚከበርበት፣ በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ፣ እስራኤል ሁሉ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ሲታይ፣ ይህን ሕግ በእነርሱ ፊት በጆሯቸው ታነብበዋለህ። ይሰሙና አምላካችሁን እግዚአብሔርን መፍራት ይማሩ ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችንና በከተሞችህ የሚኖረውንም መጻተኛ ሰብስብ። ዮርዳኖስን ተሻግረህ በምትወርሷት ምድር፣ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ፣ ይህን ሕግ የማያውቁት ልጆቻቸውም መስማትና አምላካችሁን እግዚአብሔርን መፍራት ሊማሩ ይገባቸዋል።” እግዚአብሔር ሙሴን፣ “እነሆ የምትሞትበት ቀን ቀርቧል፤ ትእዛዝ እንድሰጠው ኢያሱን ጥራውና ወደ መገናኛው ድንኳን ቅረቡ።” ሙሴና ኢያሱም ሄዱ፤ ወደ መገናኛው ድንኳንም ቀረቡ። እግዚአብሔርም በድንኳኑ ላይ በደመና ዐምድ ተገለጠ፤ የደመናውም ዐምድ ከድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆመ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፤ ከአባቶችህ ጋራ ልታርፍ ነው፤ ይህም ሕዝብ በሚገባበት ምድር በሚገኙ ባዕዳን አማልክት ወዲያውኑ ያመነዝራል። እኔን ይተወኛል፤ ከእነርሱም ጋራ የገባሁትን ኪዳን ያፈርሳሉ። በዚያች ቀን እቈጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፣ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፣ አምላካችን ከእኛ ጋራ ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ። ወደ ባዕዳን አማልክት በመዞር ከፈጸሙት ክፋታቸው የተነሣ፣ በዚያች ቀን ፊቴን ከእነርሱ ፈጽሞ እሰውራለሁ። “እንግዲህ ይህን መዝሙር ለራሳችሁ ጻፉ፤ ለእስራኤል ልጆችም አስተምሩ፤ ስለ እኔ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ እንዲዘምሩ አድርጉ። ወተትና ማር ወደምታፈስሰውና ለአባቶቻቸው በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ባመጣኋቸው ጊዜ ከበሉና ከጠገቡ፣ ከበለጸጉም በኋላ፣ እኔን ንቀው ኪዳኔንም አፍርሰው ወደ ባዕዳን አማልክት ይዞራሉ፤ እነርሱንም ያመልካሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር በደረሰባቸው ጊዜ ይህ መዝሙር ምስክር ይሆንባቸዋል፤ በዘሮቻቸው የሚረሳ አይደለምና። ወደ ማልሁላቸው ምድር ሳላስገባቸው በፊት ምን ለማድረግ እንደሚያስቡ እንኳ አስቀድሜ ዐውቃለሁ።” ስለዚህም ሙሴ ይህን መዝሙር በዚያች ቀን ጻፈ፤ ለእስራኤላውያንም አስተማራቸው። እግዚአብሔርም ለነዌ ልጅ ለኢያሱ፣ “በርታ፤ ደፋር ሁን፤ የእስራኤልን ልጆች በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ታስገባቸዋለህና፤ እኔም ከአንተ ጋራ እሆናለሁ” በማለት ትእዛዝ ሰጠው። ሙሴ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የዚህን ሕግ ቃል በመጽሐፍ ጽፎ እንዳበቃ፣ ሙሴ የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት የሚሸከሙ ሌዋውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ይህን የሕግ መጽሐፍ ውሰዱ፤ በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖር ዘንድ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር የኪዳን ታቦት አጠገብ አስቀምጡት፤ ይህም በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖራል፤