ዘዳግም 28

28
በመታዘዝ የሚገኝ በረከት
1ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፍጹም ብትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙን ሁሉ በጥንቃቄ ብትከተል፣ አምላክህ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ያደርግሃል። 2አምላክህን እግዚአብሔርን ብትታዘዝ፣ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ያንተ ይሆናሉ፤ አይለዩህምም።
3በከተማ ትባረካለህ፣ በዕርሻህም ትባረካለህ።
4የማሕፀንህ ፍሬ፣ የምድርህ አዝመራ፣ የእንስሳትህ ግልገሎች፣ የከብትህ ጥጃ፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህም ይባረካሉ።
5እንቅብህና ቡሖ ዕቃህ ይባረካሉ።
6ስትገባ ትባረካለህ፤ ስትወጣም ትባረካለህ።
7 እግዚአብሔር በአንተ ላይ የሚነሡ ጠላቶችህን በፊትህ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ በሰባት አቅጣጫም ከአንተ ይሸሻሉ።
8 እግዚአብሔር በጐተራህና እጅህ በነካው ሁሉ በረከቱን ይልካል። አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ላይ ይባርክሃል።
9የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የምትጠብቅና በመንገዱ የምትሄድ ከሆነ፣ በመሐላ በሰጠህ ተስፋ መሠረት የተቀደሰ ሕዝቡ አድርጎ ያቆምሃል፤ 10ከዚያም የምድር አሕዛብ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም። 11እግዚአብሔርም ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በማሕፀንህ ፍሬ፣ በእንስሳትህም ግልገል፣ በምድርህም ሰብል የተትረፈረፈ ብልጽግና ይሰጥሃል።
12 እግዚአብሔር ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ለመስጠትና የእጅህን ሥራ ሁሉ ለመባረክ፣ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከአንዳቸውም አትበደርም። 13እግዚአብሔርም ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በጥንቃቄ ብትጠብቅ፣ መቼውንም ቢሆን በላይ እንጂ ፈጽሞ በታች አትሆንም። 14ሌሎችን አማልክት በመከተል እነርሱን በማገልገል ዛሬ ከምሰጥህ ትእዛዞች ቀኝም ግራም አትበል።
አለመታዘዝ የሚያስከትላቸው ርግማኖች
15ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ባትታዘዝ በዛሬዋ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ሁሉ በጥንቃቄ ባትከተላቸው፣ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ ይደርሱብሃል፤ ያጥለቀልቁሃልም፦
16በከተማ ትረገማለህ፤ በዕርሻም ትረገማለህ።
17እንቅብህና ቡሖ ዕቃህ የተረገሙ ይሆናሉ።
18የማሕፀንህ ፍሬ፣ የዕርሻህ ሰብል፣ የመንጋህ ጥጆች፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህ ይረገማሉ።
19ስትገባ ትረገማለህ፤ ስትወጣም ትረገማለህ።
20እርሱን#28፥20 ዕብራይስጡ፣ እኔን ይላል። በመተው ክፉ ድርጊት ከመፈጸምህ የተነሣ፣ እስክትደመሰስ ፈጥነህም እስክትጠፋ ድረስ እጅህ በነካው ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ርግማንን፣ መደናገርንና ተግሣጽን ይሰድድብሃል። 21እግዚአብሔር ልትወርሳት ከምትገባባት ምድር ላይ እስኪያጠፋህ ድረስ በደዌ ይቀሥፍሃል። 22እግዚአብሔር እስክትጠፋ ድረስ በሚቀሥፍ ደዌ፣ ትኵሳትና ዕባጭ፣ ኀይለኛ ሙቀትና ድርቅ፣ ዋግና አረማሞ ይመታሃል። 23ከራስህ በላይ ያለው ሰማይ ናስ፣ ከእግርህ በታች ያለው ምድርም ብረት ይሆናል። 24እግዚአብሔር የምድርህን ዝናብ ወደ ዐቧራነትና ወደ ትቢያነት ይለውጠዋል፤ ይህም እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል።
25 እግዚአብሔር በጠላቶችህ ፊት እንድትሸነፍ ያደርግሃል፤ በአንድ አቅጣጫ ትመጣባቸዋለህ፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫ ከፊታቸው ትሸሻለህ፤ ለምድር መንግሥታትም ሁሉ መሸማቀቂያ ትሆናለህ። 26ሬሳህ የሰማይ አሞሮችና የምድር አራዊት ሲሳይ ይሆናል፤ በማስፈራራትም የሚያባርራቸው አይኖርም። 27እግዚአብሔር በማትድንበት በግብጽ ብጉንጅ፣ በዕባጭ፣ በሚመግል ቍስልና በዕከክ ያሠቃይሃል። 28እግዚአብሔር በእብደት፣ በዕውርነትና ግራ በማጋባት ያስጨንቅሃል። 29በእኩለ ቀን፣ በጨለማ እንዳለ ዕውር በዳበሳ ትሄዳለህ። የምታደርገው ሁሉ አይሳካልህም። በየዕለቱ ትጨቈናለህ፤ ትመዘበራለህም፤ የሚታደግህ አይኖርም።
30ሚስት ለማግባት ልጃገረድ ታጫለህ፤ ሌላው ግን ወስዶ ይደፍራታል። ቤት ትሠራለህ፣ ግን አትኖርበትም። ወይን ትተክላለህ፤ ፍሬውን ግን አትበላም። 31በሬህ ዐይንህ እያየ ይታረዳል፤ ከሥጋውም አንዳች አትቀምስም። አህያህም በግድ ይወሰድብሃል፤ አይመለስልህም። በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚያስጥላቸውም አይኖርም። 32ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለባዕድ ሕዝብ ይሰጣሉ፤ እጅህንም ለማንሣት ዐቅም ታጣለህ፤ ከዛሬ ነገ ይመጣሉ በማለትም ዐይኖችህ ሁልጊዜ እነርሱን በመጠባበቅ ይደክማሉ። 33የምድርህንና የድካምህን ፍሬ ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ ዕድሜ ልክህን በጭካኔና በጭቈና ከመኖር በቀር የሚተርፍህ ነገር አይኖርም። 34የምታየው ሁሉ ያሳብድሃል። 35እግዚአብሔር ከእግርህ ጥፍር እስከ ራስህ ጠጕር በሚዛመት፣ ሊድን በማይችልና በሚያሠቃይ ቍስል ጕልበትህንና እግርህን ይመታሃል።
36 እግዚአብሔር አንተንና በላይህ ያነገሥኸውን ንጉሥ፣ አንተና አባቶችህ ወደማታውቁት ሕዝብ ይወስዳችኋል፤ ከዚያም ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ። 37እግዚአብሔር እንድትገባ በሚያደርግበት ምድር ለአሕዛብ ሁሉ መሸማቀቂያ፣ ማላገጫና መዘባበቻ ትሆናለህ።
38በዕርሻ ላይ ብዙ ዘር ትዘራለህ፤ አንበጣ ስለሚበላው ግን፣ የምትሰበስበው ጥቂት ይሆናል። 39ወይን ትተክላለህ፤ ትንከባከበዋለህ፤ ነገር ግን ትል ይበላዋልና ዘለላውን አትሰበስብም። 40በአገርህ ምድር ሁሉ የወይራ ዛፍ ይኖርሃል፤ ፍሬው ስለሚረግፍብህ ግን፣ ዘይቱን አትጠቀምበትም። 41ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትወልዳለህ፤ ነገር ግን በምርኮ ስለሚወሰዱ፣ ዐብረውህ አይኖሩም። 42ዛፍህንና የምድርህን ሰብል ሁሉ የአንበጣ መንጋ ይወርረዋል።
43በመካከልህ የሚኖር መጻተኛ ከአንተ በላይ ከፍ ከፍ ሲል፣ አንተ ግን ዝቅ ዝቅ ትላለህ። 44እርሱ ያበድርሃል እንጂ አንተ አታበድረውም። እርሱ ራስ ይሆናል፤ አንተ ግን ጅራት ትሆናለህ።
45እነዚህ ርግማኖች ሁሉ በአንተ ላይ ይመጣሉ፤ አምላክህን እግዚአብሔርን ስላልታዘዝህና የሰጠህን ትእዛዝና ሥርዐት ስላልጠበቅህ እስክትጠፋ ድረስ ይከተሉሃል፤ ይወርዱብሃልም። 46ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም ምልክትና መገረም ይሆናሉ። 47በብልጽግና ጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን በደስታና በሐሤት ስላላገለገልኸው፣ 48በራብና በጥም፣ በእርዛትና በከፋ ድኽነት እግዚአብሔር የሚያስነሣብህን ጠላቶችህን ታገለግላለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በዐንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭንብሃል።
49 እግዚአብሔር እንደ ንስር ፈጥኖ የሚወርድንና ቋንቋውን የማታውቀውን ሕዝብ እጅግ ሩቅ ከሆነ፣ ከምድርም ዳርቻ ያስነሣብሃል፤ 50ሽማግሌ የማያከብር፣ ለብላቴና የማይራራ፣ ሲያዩት የሚያስፈራ ሕዝብ ነው። 51እስክትጠፋም ድረስ የእንስሳትህን ግልገልና የምድርህን ሰብል ይበላል፤ እስኪያጠፋህም ድረስ እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅ ሆነ ዘይት፣ የመንጋህን ጥጃ ሆነ የበግና የፍየል መንጋህን ግልገል አያስቀርልህም። 52የምትታመንባቸውን ታላላቅ የተመሸጉ ቅጥሮች እስኪወድቁ ድረስ በመላው አገርህ ያሉትን ከተሞችህን ሁሉ ይከብባል፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ያሉትን ከተሞች በሙሉ ይወርራቸዋል።
53ጠላቶችህ ከብበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ ከሥቃይ የተነሣ፣ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን፣ የወገብህ ፍሬ የሆኑትን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ። 54ሌላው ይቅርና በመካከልህ በጣም ደግና ርኅሩኅ የሆነው ሰው እንኳ ለገዛ ወንድሙ ወይም ለሚወድዳት ሚስቱ ወይም ለተረፉት ልጆቹ አይራራላቸውም። 55ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ላይም ቅንጣት ታኽል እንኳ ከእነርሱ ለአንዱ አያቀምስም፤ ከተሞችህ ሁሉ በመከበባቸው ጠላቶችህ ከሚያደርሱብህ ሥቃይ የተነሣ ለርሱ የቀረለት ይህ ብቻ ነውና። 56በመካከልህ ተለሳልሳና ተቀማጥላ የምትኖር፣ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ፣ እግሯን ዐፈር ነክቶት የማያውቅ ሴት፣ የምትወድደውን ባሏን፣ የገዛ ወንድ ወይም ሴት ልጆቿን ትንቃለች። 57ከማሕፀኗ የወጣውን እንግዴ ልጇንና የምትወልዳቸውን ሕፃናት ትጠየፋለች፤ ይህን የምታደርገውም በመከራው ወቅት ጠላቶችህ ከተሞችህን ከብበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ እነርሱን ደብቃ ለመብላት ስትል ነው።
58በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የዚህን ሕግ ቃሎች በጥንቃቄ ባትከተልና አስደናቂና አስፈሪ የሆነውን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ስም ባታከብር፣ 59እግዚአብሔር አስፈሪ መቅሠፍት፣ አስጨናቂና ለብዙ ጊዜ የሚቈይ መዓት፣ አሠቃቂና በቀላሉ የማይወገድ ደዌ በአንተና በዘሮችህ ላይ ይልክባችኋል። 60የምትፈራቸውንም የግብጽ በሽታዎች ሁሉ ያመጣብሃል፤ በአንተም ላይ ይጣበቃሉ። 61ደግሞም እግዚአብሔር በዚህ የሕግ መጽሐፍ ያልተጻፈውን ማንኛውንም ዐይነት ደዌና መከራ እስክትጠፋ ድረስ ያመጣብሃል። 62ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዛችሁ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችሁ የነበራችሁት እናንተ ጥቂት ብቻ ትቀራላችሁ። 63እግዚአብሔር እናንተን በማበልጸግና ቍጥራችሁን በማብዛት ደስ እንደ ተሠኘ፣ እናንተን በማጥፋትና በመደምሰስም ደስ ይለዋል፤ ልትወርሷት ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ።
64ከዚያም እግዚአብሔር ከአንዱ የምድር ዳርቻ እስከ ሌላው ዳርቻ በሕዝቦች ሁሉ መካከል ይበትንሃል። በዚያ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቋቸውን ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ። 65በእነዚያ ሕዝቦች መካከል ዕረፍት አታገኝም፤ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ ቦታ አይኖርም። እዚያም እግዚአብሔር የሚጨነቅ አእምሮ፣ በናፍቆት የሚደክም ዐይንና ተስፋ የሚቈርጥ ልብ ይሰጥሃል። 66ቀንም ሆነ ሌሊት በፍርሀት እንደ ተዋጥህ፣ ሕይወትህ ዋስትና ሳታገኝ፣ ዘወትር በሥጋት ትኖራለህ። 67ልብህ በፍርሀት ከመሞላቱና ዐይንህ ከሚያየው የተነሣ፣ ሲነጋ፣ “ምነው አሁን በመሸ!” ሲመሽ ደግሞ፣ “ምነው አሁን በነጋ!” ትላለህ። 68ዳግመኛ አትመለስባትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብጽ ይመልስሃል። እዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሮች እንድትሆኗቸው ለጠላቶቻችሁ ለመሸጥ ራሳችሁን ታቀርባላችሁ፤ የሚገዛችሁ ግን አይኖርም።

Currently Selected:

ዘዳግም 28: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ