ዘዳግም 24

24
1አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባ በኋላ፣ አሳፋሪ ነገር አግኝቶባት ባይደሰትባት፣ የፍች ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ይስደዳት። 2ከቤቱ ከወጣች በኋላ ሌላ ባል ብታገባ፣ 3ሁለተኛ ባሏም እንደዚሁ ጠልቷት የፍች ወረቀት በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ቢሰድዳት ወይም ቢሞት፣ 4ከዚያ በኋላ የፈታት የመጀመሪያ ባሏ፣ የረከሰች በመሆኗ እንደ ገና መልሶ ሊያገባት አይችልም፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው። አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ ኀጢአት አታምጣ።
5አዲስ ሚስት በቅርብ ጊዜ ያገባ ሰው፣ ለጦርነት አይሂድ፤ ወይም ሌላ ሥራ እንዲሠራ አይገደድ። ለአንድ ዓመት ነጻ ሆኖ ቤቱ ይቈይ፤ ያገባትን ሚስቱን ደስ ያሰኛት።
6ወፍጮና መጁን ወይም መጁንም እንኳ ቢሆን፣ የብድር መያዣ አድርገህ አትውሰድ፤ የሰውን ነፍስ መያዣ አድርጎ መውሰድ ይሆናልና።
7አንድ ሰው ከእስራኤላውያን ወንድሞቹ አንዱን ፈንግሎ በመውሰድ ባሪያ ሲያደርገው ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፣ ፈንጋዩ ይሙት። ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።
8የለምጽ ደዌን#24፥8 ዕብራይስጡ ለምጽን ብቻ ሳይሆን ቈዳን የሚያጠቁትን ማንኛውንም ዐይነት በሽታዎች ያመለክታል። በተመለከተ ሌዋውያን ካህናት የሚሰጡህን መመሪያ በትክክል ለመፈጸም ጥንቃቄ አድርግ። እኔ ለእነርሱ የሰጠሁትን ትእዛዝ በጥንቃቄ ተከተል። 9ከግብጽ ከወጣችሁ በኋላ በመንገድ ላይ ሳላችሁ አምላክህ እግዚአብሔር በማርያም ላይ ያደረገባትን አስታውሱ።
10ማንኛውንም ነገር ለባልንጀራህ ስታበድር መያዣ አድርጎ የሚሰጥህን ለመቀበል ወደ ቤቱ አትግባ። 11አንተ ከውጭ ሆነህ ጠብቅ፤ ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ከቤት ያምጣልህ። 12ሰውየው ድኻ ከሆነ፣ መያዣውን ከአንተ ዘንድ አታሳድርበት። 13መደረቢያውን ለብሶት እንዲያድር ፀሓይ ሳትጠልቅ መልስለት። ከዚያም ያመሰግንሃል፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊትም የጽድቅ ሥራ ሆኖ ይቈጠርልሃል።
14ችግረኛና ድኻ የሆነውን የምንዳ ሠራተኛ እስራኤላዊ ወንድምህም ሆነ፣ ከከተሞችህ በአንዲቱ የሚኖረውን መጻተኛ አትበዝብዘው፤ 15የሠራበትን ሒሳብ በዕለቱ፣ ፀሓይ ሳትጠልቅ ክፈለው፤ ድኻ በመሆኑ በጕጕት ይጠባበቀዋልና። አለዚያ ወደ እግዚአብሔር ይጮኽና ኀጢአት ይሆንብሃል።
16አባቶች በልጆቻቸው፣ ልጆችም በአባቶቻቸው አይገደሉ፤ እያንዳንዱ በራሱ ኀጢአት ይገደል።
17ለመጻተኛው ወይም አባት ለሌለው ልጅ ፍትሕ አትንፈገው፤ የመበለቲቱንም መደረቢያ መያዣ አታድርግ። 18አንተም በግብጽ ባሪያ እንደ ነበርህና አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ይህን እንድታደርግ ያዘዝሁህ ለዚህ ነው።
19የዕርሻህን ሰብል በምታጭድበት ጊዜ፣ ተረስቶ የቀረ ነዶ ቢኖር፣ ያን ለመውሰድ ተመልሰህ አትሂድ። አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነዶውን ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። 20የወይራ ዛፍህን ፍሬ በምታራግፍበት ጊዜ፣ በየቅርንጫፉ ላይ የቀረውን ለመቃረም ተመልሰህ አትሂድ፤ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። 21የወይን ተክልህን ፍሬ ስትሰበስብ ቃርሚያውን ለመሰብሰብ አትመለስበት፤ የቀረውን ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። 22በግብጽ ባሪያ እንደ ነበርህ አስታውስ፤ ይህን እንድታደርግ ያዘዝሁህ ለዚህ ነው።

Currently Selected:

ዘዳግም 24: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ