ዘዳግም 19:14-21

ዘዳግም 19:14-21 NASV

አምላክህ እግዚአብሔር እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ውስጥ ለአንተ በሚተላለፍልህ ርስት ላይ የቀድሞ ሰዎች ያስቀመጡትን የባልንጀራህን የድንበር ምልክት አታንሣ። በማንኛውም ወንጀል ወይም ሕግ በመተላለፍ ሰውን ጥፋተኛ ለማድረግ፣ አንድ ምስክር አይበቃም፤ ነገር በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች የምስክር አፍ መረጋገጥ አለበት። ተንኰለኛ የሆነ ምስክር አንድን ሰው በሐሰት ቢከስስ፣ ክርክሩ የሚመለከታቸው ሁለቱ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት፣ በዚያ ወቅት በሚያገለግሉት ካህናትና ፈራጆች ፊት ይቁሙ። ፈራጆችም ጕዳዩን በጥልቅ ይመርምሩት፤ ያም ምስክር በወንድሙ ላይ በሐሰት የመሰከረ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ በወንድሙ ላይ ለማድረግ ያሰበውን በርሱ ላይ አድርጉበት፤ ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ። የቀሩትም ሰዎች ይህን ሰምተው ይፈራሉ፤ እንዲህ ያለው ክፉ ነገርም ለወደፊቱ በመካከልህ ከቶ አይደገምም። ርኅራኄ አታድርግ፤ ሕይወት በሕይወት፣ ዐይን በዐይን፣ ጥርስ በጥርስ፣ እጅ በእጅ፣ እግር በእግር ይመለስ።