ዘዳግም 19:1-13

ዘዳግም 19:1-13 NASV

አምላክህ እግዚአብሔር ምድራቸውን ለአንተ የሚሰጥባቸውን አሕዛብ በሚደመስሳቸው ጊዜና አንተም እነርሱን አስለቅቀህ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸው በምትቀመጥበት ጊዜ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር አማካይ ስፍራ፣ ሦስት ከተሞችን ለራስህ ለይ። ሰው የገደለ ሁሉ እንዲሸሽባቸው አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር መንገዶችን ሠርተህ፣ በሦስት ክፈላቸው። በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ገድሎ ሕይወቱን ለማትረፍ ለሚሸሽ ሰው መመሪያው የሚከተለው ነው። እነሆ፤ አንድ ሰው ከባልንጀራው ጋራ ዕንጨት ለመቍረጥ ወደ ጫካ ቢሄድ፣ ዛፉን ለመጣል መጥረቢያውን በሚሰነዝርበት ጊዜ ብረቱ ከእጀታው ወልቆ ባልንጀራውን በመምታት ቢገድለው፣ ያ ሰው ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ ሕይወቱን ማትረፍ ይችላል። አለዚያ በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ቢገድል፣ መንገዱ ረዥም ከሆነ ደም ተበቃዩ በንዴት ተከታትሎ ይደርስበትና መገደል የማይገባውን ሰው ሊገድል ይችላል። ሦስት ከተሞችን ለራስህ እንድትለይ ያዘዝሁህ በዚሁ ምክንያት ነው። ለአባቶችህ በመሐላ በገባላቸው ቃል መሠረት፣ አምላክህ እግዚአብሔር ወሰንህን ሲያሰፋውና ለእነርሱ በሰጣቸው መሠረት ምድሪቱን ሁሉ ሲሰጥህ፣ አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድድና ምን ጊዜም በመንገዱ እንድትሄድ ዛሬ የማዝዝህን እነዚህን ሕግጋት ሁሉ በጥንቃቄ የምትጠብቅ ከሆነ፣ በእነዚህ ላይ ሌሎች ሦስት ከተሞችን ትጨምራለህ። አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር የንጹሕ ሰው ደም እንዳይፈስስና በሚፈስሰውም ደም በደለኛ እንዳትሆን ይህን አድርግ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢጠላው፣ አድፍጦ ጥቃት ቢያደርስበት፣ ቢገድለውና ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ፣ የሚኖርባት ከተማ ሽማግሌዎች ሰው ልከው ከከተማው ያስመጡት፤ እንዲገድለውም ለደም ተበቃዩ አሳልፈው ይስጡት። አትራራለት፤ ነገር ግን መልካም እንዲሆንልህ የንጹሑን ደም በደል ከእስራኤል አስወግድ።