ዘዳግም 1:29-46

ዘዳግም 1:29-46 NASV

እኔም አልኋችሁ፤ “አትሸበሩ፤ አትፍሯቸውም። በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ዐይናችሁ እያየ በግብጽ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፣ አሁንም ለእናንተ ይዋጋል፤ በምድረ በዳው እንደ አደረገው ሁሉ። በዚያም አባት ልጁን እንደሚሸከም፣ እናንተን አምላካችሁ እግዚአብሔር እዚህ ስፍራ እስክትደርሱ በመጣችሁበት መንገድ ሁሉ እንዴት እንደ ተሸከማችሁ አይታችኋል።” ይህም ሆኖ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር አልታመናችሁም፤ በጕዞ ላይ ሳላችሁ የምትሰፍሩባቸውን ቦታዎች ለመፈለግና የምትሄዱበትን መንገድ ለማሳየት እርሱ ሌሊት በእሳት፣ ቀን በደመና ይመራችሁ ነበር። እግዚአብሔርም እናንተ ያላችሁትን በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ ማለም፤ “ለቀደሙት አባቶቻችሁ ለመስጠት የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር፣ ከዚህ ክፉ ትውልድ አንድም ሰው አያያትም፤ ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በቀር የሚያያት የለም፤ እርሱ ያያታል፤ እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ ስለ ተከተለ፣ የረገጣትን ምድር ለርሱና ለዘሮቹ እሰጣለሁ።” በእናንተ ምክንያት እግዚአብሔር እኔን ተቈጥቶ እንዲህ አለኝ፤ “አንተም ብትሆን አትገባባትም። ረዳትህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ይገባባታል፤ ምድሪቱን እንዲወርሱ እስራኤልን የሚመራ እርሱ ስለ ሆነ፣ አበረታታው። ይማረካሉ ያላችኋቸው ታናናሾች፣ ክፉና በጎውን ለይተው የማያውቁት ልጆቻችሁ ምድሪቱን ይገቡባታል፤ ለእነርሱም እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሷታል። እናንተ ግን፣ ተመልሳችሁ ወደ ቀይ ባሕር የሚወስደውን መንገድ ይዛችሁ ወደ ምድረ በዳው ተጓዙ።” እናንተ፣ “በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ሠርተናል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ባዘዘንም መሠረት ወጥተን እንዋጋለን” ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ወደ ተራራማው አገር መሄድ ቀላል መስሎ ስለ ታያችሁ፣ እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያችሁን ታጥቃችሁ ተነሣችሁ። እግዚአብሔር ግን፣ “ ‘እኔ ከእናንተ ጋራ አልሆንምና ወጥታችሁ እንዳትዋጉ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትነሣላችሁ’ ብለህ ንገራቸው” አለኝ። እኔም ነገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላደመጣችሁም፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐምፃችሁ፣ በትዕቢታችሁ ወደ ተራራማው አገር ዘመታችሁ። በእነዚያ በተራራማው አገር የሚኖሩት አሞራውያን ሊወጓችሁ ወጡ፤ እንደ ንብ ሰራዊትም ሆነው አባረሯችሁ፤ ከሴይር አንሥቶ እስከ ሖርማ ድረስ አሳድደው መቷችሁ። እናንተም ተመልሳችሁ መጥታችሁ በእግዚአብሔር ፊት አለቀሳችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ልቅሷችሁን አልሰማም፤ አላደመጣችሁምም። ስለዚህ ያን ያህል ጊዜ በማጥፋት በቃዴስ ብዙ ቀን ቈያችሁ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}