ዘዳግም 1:19-35

ዘዳግም 1:19-35 NASV

ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር ባዘዘን መሠረት ከኮሬብ ተነሥተን እንዳያችሁት በዚያ ጭልጥ ባለና በሚያስፈራ ምድረ በዳ ዐልፈን፣ በኰረብታማው በአሞራውያን አገር በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን። እኔም፣ እንዲህ አልኋችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ደርሳችኋል፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ሰጥቷችኋል፤ አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በነገራችሁ መሠረት ውጡ፤ ውረሷትም፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡም።” ከዚያም ሁላችሁ ወደ እኔ መጥታችሁ፣ “ምድሪቱን እንዲሰልሉልን ሰዎች አስቀድመን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያ የሚያደርሰንን መንገድና የምንሄድባቸውን ከተሞች በማጥናት ተመልሰው ይነግሩናል” አላችሁ። ይህም ሐሳብ መልካም መስሎ ታየኝ፤ እኔም ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በማድረግ ከእናንተ ዐሥራ ሁለት ሰዎች መረጥሁ። እነርሱም ተነሥተው ወደ ኰረብታማው አገር ከወጡ በኋላ ወደ ኤሽኮል ሸለቆ መጥተው ምድሪቱን ሰለሉ። ከምድሪቱም ፍሬ ወደ እኛ ይዘው በመምጣት፣ “አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጠን ምድር መልካም ናት” ብለው ነገሩን። እናንተ ግን ለመውጣት ፈቃደኞች አልነበራችሁም፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ። በየድንኳኖቻችሁ ሆናችሁ እንዲህ ስትሉ አጕረመረማችሁ፤ “እግዚአብሔር ጠልቶናል፤ ስለዚህም ከግብጽ ያወጣን አሞራውያን እንዲያጠፉን በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ነው። ታዲያ ወዴት መሄድ እንችላለን? ወንድሞቻችን፣ ‘ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎችና ቁመተ ረዣዥሞች፣ ከተሞቹም ትልልቆችና እስከ ሰማይ በሚደርስ ቅጥር የታጠሩ ናቸው፤ እንዲያውም በዚያ የዔናቅን ልጆች አይተናቸዋል’ ሲሉ እንድንፈራ አድርገውናል።” እኔም አልኋችሁ፤ “አትሸበሩ፤ አትፍሯቸውም። በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ዐይናችሁ እያየ በግብጽ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፣ አሁንም ለእናንተ ይዋጋል፤ በምድረ በዳው እንደ አደረገው ሁሉ። በዚያም አባት ልጁን እንደሚሸከም፣ እናንተን አምላካችሁ እግዚአብሔር እዚህ ስፍራ እስክትደርሱ በመጣችሁበት መንገድ ሁሉ እንዴት እንደ ተሸከማችሁ አይታችኋል።” ይህም ሆኖ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር አልታመናችሁም፤ በጕዞ ላይ ሳላችሁ የምትሰፍሩባቸውን ቦታዎች ለመፈለግና የምትሄዱበትን መንገድ ለማሳየት እርሱ ሌሊት በእሳት፣ ቀን በደመና ይመራችሁ ነበር። እግዚአብሔርም እናንተ ያላችሁትን በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ ማለም፤ “ለቀደሙት አባቶቻችሁ ለመስጠት የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር፣ ከዚህ ክፉ ትውልድ አንድም ሰው አያያትም፤

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}