የባቢሎን ንጉሥ ቤልሻዛር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በዐልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ ሕልም ዐለመ፤ ራእይም አየ፤ የሕልሙንም ዋና ሐሳብ ጻፈው። ዳንኤል እንዲህ አለ፤ “አራቱ የሰማይ ነፋሳት ታላቁን ባሕር ሲያናውጡት ሌሊት በራእይ አየሁ። እርስ በርሳቸው የማይመሳሰሉ አራት ታላላቅ አራዊት ከባሕሩ ወጡ። “የመጀመሪያው፣ አንበሳ ይመስል ነበር፤ የንስርም ክንፎች ነበሩት፤ ክንፎቹ እስኪነቃቀሉ ድረስ ተመለከትሁ፤ እንደ ሰው በሁለት እግሩ እንዲቆም ከምድር ከፍ ከፍ ተደረገ፤ የሰውም ልብ ተሰጠው። “እነሆም፤ ሁለተኛው አውሬ ድብ ይመስል ነበር፤ በአንድ ጐኑ ከፍ ብሏል፤ በአፉ ውስጥ በጥርሶቹ መካከል ሦስት የጐድን ዐጥንቶች ነበሩት። እርሱም፤ ‘ተነሥ፤ እስክትጠግብ ድረስ ሥጋ ብላ!’ ተባለ። “ከዚያ በኋላ ተመለከትሁ፤ በፊቴ ነብር የሚመስል ሌላ አውሬ ነበር፤ በጀርባውም በኩል የወፍ ክንፍ የሚመስሉ አራት ክንፎች ነበሩት፤ ይህ አውሬ አራት ራስ ነበረው፤ ለመግዛትም ሥልጣን ተሰጠው። “ከዚህ በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ በፊቴም የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ በጣም ኀይለኛ የሆነ አራተኛ አውሬ ነበር፤ ትልልቅ የብረት ጥርሶች ነበሩት፤ ያደቅቅና ይበላ፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ ይረጋግጥ ነበር። ከርሱ በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየ ሲሆን፣ ዐሥር ቀንዶች ነበሩት። “ስለ ቀንዶቹ ሳስብ ሳለሁ፣ ከመካከላቸው አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ ብቅ ሲል አየሁ፤ ከመጀመሪያዎቹ ቀንዶች ሦስቱ ከፊቱ ተነቃቀሉ፤ ይህም ቀንድ የሰው ዐይኖችን የሚመስሉ ዐይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበረው። “እኔም ስመለከት፣ “ዙፋኖች ተዘረጉ፤ ጥንታዌ ጥንቱም ተቀመጠ፤ ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፤ የራሱም ጠጕር እንደ ጥጥ ነጭ ነበረ፤ ዙፋኑ የእሳት ነበልባል፣ መንኰራኵሮቹም ሁሉ እንደሚነድድ እሳት ነበሩ። የእሳት ወንዝ፣ ከፊት ለፊቱ ፈልቆ ይፈስስ ነበር፤ ሺሕ ጊዜ ሺሖች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል፤ የፍርድ ጉባኤ ተሰየመ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። “ቀንዱም ከሚናገረው የትዕቢት ቃል የተነሣ፣ መመልከቴን ቀጠልሁ፤ አውሬው እስኪታረድና አካሉ ደቅቆ ወደሚንበለበለው እሳት እስኪጣል ድረስ ማየቴን አላቋረጥሁም። ሌሎቹም አራዊት ሥልጣናቸው ተገፍፎ ነበር፤ ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜና ወቅት በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው። “ሌሊት ባየሁት ራእይ፣ የሰውን ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና ጋራ ሲመጣ አየሁ፤ ወደ ጥንታዌ ጥንቱ መጣ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው። “እኔ ዳንኤል በመንፈሴ ታወክሁ፤ ያየሁትም ራእይ እጅግ አስጨነቀኝ። በዚያ ከቆሙት ወደ አንዱ ቀርቤ፣ የዚህ ሁሉ እውነተኛ ትርጕም ምን እንደ ሆነ ጠየቅሁት። “እርሱም መለሰልኝ፤ የእነዚህንም ነገሮች ትርጕም እንዲህ ሲል ነገረኝ፤ ‘አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ መንግሥታት ናቸው፤ ነገር ግን የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፤ ለዘላለምም ይይዙታል፤ አዎን፤ ለዘላለም ይይዙታል።’ “ከዚያም የሚያደቅቀውንና የሚበላውን፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ የሚረጋግጠውን፣ የብረት ጥርሶችና የናስ ጥፍሮች የነበሩትን፣ ከሌሎቹ አራዊት የተለየና እጅግ አስፈሪ የሆነውን የአራተኛውን አውሬ እውነተኛ ትርጕም ማወቅ ፈለግሁ። ደግሞም በራሱ ላይ ስላሉት ዐሥር ቀንዶች፣ ከመካከላቸው ብቅ ስላለው ቀንድና ከዚሁ ቀንድ ፊት ስለ ተነቃቀሉት ሦስት ቀንዶች፣ እንደዚሁም ከሌሎች ስለ በለጠው የሰው ዐይኖች የሚመስሉ ዐይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ስለ ነበሩት ስለዚሁ ቀንድ ማወቅ ፈለግሁ። እነሆም፤ ይህ ቀንድ በቅዱሳን ላይ ጦርነት ዐውጆ አሸነፋቸው፤ ይህም የሆነው ጥንታዌ ጥንቱ እስኪመጣና ለልዑሉ ቅዱሳን እስኪፈርድላቸው ድረስ ነበር፤ ከዚያም የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን የሚወርሱበት ዘመን መጣ። “እርሱም እንዲህ አለኝ፣ ‘አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሣ አራተኛው መንግሥት ነው። ከሌሎች መንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፤ መላውንም ምድር እየረገጠና እያደቀቀ ይበላል። ዐሥሩ ቀንዶች ከዚህ መንግሥት የሚወጡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከዚያም በኋላ ከእነርሱ የተለየ ሌላ ንጉሥ ይነሣል፤ ሦስቱንም ነገሥታት ያንበረክካል። በልዑል ላይ የዐመፅ ቃል ይናገራል፤ የልዑልንም ቅዱሳን ያስጨንቃል፤ ለበዓላት የተመደበውን ጊዜና ሕግን ለመለወጥ ይሞክራል፤ ቅዱሳንም ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመን እኩሌታም ለርሱ ዐልፈው ይሰጣሉ። “ ‘ነገር ግን የፍርድ ዙፋን ይዘረጋል፤ ሥልጣኑም ይወሰድበታል፤ ፈጽሞ ለዘላለም ይደመሰሳል። ከዚያም ከሰማይ በታች ያሉ መንግሥታት ልዕልና፣ ሥልጣንና ታላቅነት ለልዑሉ ሕዝብ፣ ለቅዱሳን ይሰጣል። መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ይሆናል፤ ገዦች ሁሉ ያመልኩታል፤ ይታዘዙታልም።’ “የነገሩ ፍጻሜ ይህ ነው፤ እኔም ዳንኤል በሐሳቤ እጅግ ተጨነቅሁ፤ መልኬም ተለዋወጠ፤ ይሁን እንጂ ነገሩን በልቤ ጠበቅሁት።”
ዳንኤል 7 ያንብቡ
ያዳምጡ ዳንኤል 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዳንኤል 7:1-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች