ዳንኤል 6:4-9

ዳንኤል 6:4-9 NASV

በዚህ ምክንያት የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ ዳንኤል በሚያከናውነው የመንግሥት ሥራ ሊከስሱት ሰበብ ፈለጉ፤ ነገር ግን አላገኙበትም፤ ዳንኤል ታማኝ፣ ጠንቃቃና በሥራው እንከን የሌለበት ስለ ነበር፣ በርሱ ላይ ስሕተት ሊያገኙ አልቻሉም። እነዚህም ሰዎች፣ “ከአምላኩ ሕግ ጋራ በተያያዘ ጕዳይ ካልሆነ በቀር፣ ይህን ዳንኤልን የምንከስበት ምንም ሰበብ አናገኝበትም” አሉ። ከዚያም የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! ንጉሥ ሆይ፤ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ማንም ሰው ወደ ሌላ ሰውም ሆነ ወደ ሌላ አምላክ መጸለይ እንደሌለበት ንጉሡ ዐዋጅ እንዲያወጣ፣ ትእዛዙም እንዲፈጸም፣ ይህንም የተላለፈ ወደ አንበሶች ጕድጓድ እንዲጣል፣ የመንግሥት የበላይ አስተዳዳሪዎች፣ መኳንንት፣ መሳፍንት፣ አማካሪዎችና አገረ ገዦች ሁሉ በአንድነት ተስማምተዋል። ንጉሥ ሆይ፤ ይህን ዐዋጅ አውጣ፤ እንደማይሻረውና እንደማይለወጠው የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንዲሆን ትእዛዙን በጽሑፍ አድርገው።” ስለዚህ ንጉሥ ዳርዮስ ዐዋጁ ተጽፎ እንዲወጣ አደረገ።