ዳንኤልንም ወደ ንጉሡ አቀረቡት፤ ንጉሡም እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ማርኮ ካመጣቸው መካከል አንዱ የሆንኸው ዳንኤል አንተ ነህን? የአማልክት መንፈስ በውስጥህ እንዳለ፣ ዕውቀት፣ ማስተዋልና ልዩ ጥበብ እንዳለህ ሰምቻለሁ። ይህን ጽሕፈት አንብበው ትርጕሙ ምን እንደ ሆነ ይነግሩኝ ዘንድ ጠቢባንና አስማተኞች በፊቴ ቀርበው ነበር፤ ነገር ግን ሊገልጡት አልቻሉም። አንተ ግን መተርጐምና አስቸጋሪ የሆነውን ነገር መፍታት እንደምትችል ሰምቻለሁ። ይህን ጽሕፈት አንብበህ ትርጕሙን ብትነግረኝ፣ ሐምራዊ መጐናጸፊያ ያለብሱሃል፤ የወርቅ ሐብል በዐንገትህ ያጠልቁልሃል፤ የመንግሥት ሦስተኛ ገዥም ትደረጋለህ።” ዳንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ስጦታዎችህን ለራስህ አድርግ፤ ሽልማቶችህንም ለሌላ ሰው ስጥ፤ ይሁን እንጂ ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነብባለሁ፤ ትርጕሙ ምን እንደ ሆነም እነግረዋለሁ። “ንጉሥ ሆይ፤ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር ገናናነትንና ታላቅነትን፣ ክብርንና ግርማን ሰጠው። ከሰጠው ታላቅ ሥልጣን የተነሣ ሕዝቦችና መንግሥታት፣ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችም ሁሉ ተንቀጠቀጡለት፤ ፈሩትም። ንጉሡም ሊገድል የፈለገውን ይገድል፣ ሊያድን የፈለገውን ያድን፣ ሊሾም የፈለገውን ይሾም፣ ሊያዋርድ የፈለገውንም ያዋርድ ነበር። ነገር ግን ልቡ በትዕቢት በጸናና በእብሪት በተሞላ ጊዜ ከዙፋኑ ተወገደ፤ ክብሩም ተገፈፈ። ከሰው መካከል ተሰደደ፤ የእንስሳም አእምሮ ተሰጠው፤ ከዱር አህዮች ጋራ ኖረ፤ እንደ ከብትም ሣር በላ፤ ልዑል አምላክ በሰዎች መንግሥታት ላይ እንደሚገዛና እነርሱንም ለወደደው እንደሚሰጥ እስኪያውቅ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ። “ቤልሻዛር ሆይ፤ አንተ ልጁ ሆነህ ይህን ሁሉ ብታውቅም፣ ራስህን ዝቅ አላደረግህም፤ ይልቁንም በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ፣ ራስህን ከፍ ከፍ አደረግህ፤ የመቅደሱን መጠጫዎች አስመጣህ፤ አንተና መኳንንትህ፣ ሚስቶችህና ቍባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፤ ማየት፣ መስማት፣ ማስተዋልም የማይችሉትን የብርና የወርቅ፣ የናስና የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገንህ። ሕይወትህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ ግን አላከበርህም። ስለዚህ እርሱ ጽሕፈቱን የጻፈውን እጅ ላከ። “የተጻፈውም ጽሕፈት፣ ‘ማኔ፣ ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ’ ይላል። “የቃሉም ትርጕም ይህ ነው፤ “ ማኔ ማለት አምላክ የመንግሥትህን ዘመን ቈጠረው፤ ወደ ፍጻሜም አደረሰው ማለት ነው። “ ቴቄል ማለት በሚዛን ተመዘንህ፤ ቀለህም ተገኘህ፣ ማለት ነው። “ ፋሬስ ማለት መንግሥትህ ተከፈለ፣ ለሜዶናውያንና ለፋርስ ሰዎች ተሰጠ ማለት ነው።”
ዳንኤል 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ዳንኤል 5
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዳንኤል 5:13-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች