ዳንኤል 5:1-12

ዳንኤል 5:1-12 NASV

ንጉሥ ቤልሻዛር ለሺሕ መኳንንቱ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በሺሑም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር። ቤልሻዛር የወይን ጠጁን እየጠጣ ሳለ፣ አባቱ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ያመጣቸውን የወርቅና የብር መጠጫዎችን እርሱና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቍባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ እንዲያመጡለት አዘዘ። ከዚያም በኢየሩሳሌም ከነበረው ከአምላክ ቤተ መቅደስ የተወሰዱትን የወርቅ መጠጫዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቍባቶቹም ጠጡባቸው። የወይን ጠጁንም እየጠጡ የወርቅና የብር፣ የናስ፣ የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገኑ። በድንገትም የሰው እጅ ጣቶች ታዩ፤ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በመቅረዙ ትይዩ ባለው ግድግዳ ልስን ላይ ጻፉ፤ ንጉሡም ይጽፍ የነበረውን እጅ አየ፤ በዚያ ጊዜ ንጉሡ በድንጋጤ ተሞላ፤ ፊቱም ተለዋወጠ፤ እጆቹና እግሮቹ ከዱት፤ ጕልበቶቹም ተብረከረኩ። ንጉሡም ድምፁን ከፍ አድርጎ አስማተኞችን፣ ኮከብ ቈጣሪዎችንና መተተኞችን እንዲያስገቡለት አዘዘ፤ ለባቢሎናውያኑ ጠቢባን እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ጽሕፈት አንብቦ ትርጕሙን የሚነግረኝን ሐምራዊ መጐናጸፊያ አለብሰዋለሁ፤ የወርቅ ሐብልም በዐንገቱ ላይ አጠልቅለታለሁ፤ በመንግሥቴም ላይ ሦስተኛ ገዥ ይሆናል።” ከዚያም የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ሊያነብብም ሆነ ትርጕሙ ምን እንደ ሆነ ለንጉሡ ሊነግር የሚችል ማንም አልነበረም። ንጉሥ ቤልሻዛር ከፊት ይልቅ ፈራ፤ ፊቱም እጅግ ተለወጠ፤ መኳንንቱም ግራ ገብቷቸው ተደናገጡ። ንግሥቲቱም የንጉሡንና የመኳንንቱን ድምፅ ሰምታ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገባች፤ እንዲህም አለች፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ አትደንግጥ፤ ፊትህም አይለዋወጥ! በመንግሥትህ ውስጥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት አንድ ሰው አለ፤ ይህ ሰው በአባትህ ዘመን እንደ አማልክት ጥበብና ማስተዋል፣ ዕውቀትም የሞላበት ሆኖ ተገኝቷል፤ አባትህ ንጉሥ ናቡከደነፆርም የጠንቋዮች፣ የአስማተኞች፣ የኮከብ ቈጣሪዎችና የመተተኞች አለቃ አደረገው። ንጉሡ ብልጣሶር ብሎ የጠራው ይህ ዳንኤል መልካም መንፈስ፣ ዕውቀትና ማስተዋል ያለው ሆኖ ተገኘ፤ ሕልምን የመተርጐም፣ ዕንቈቅልሽን የመፍታትና የተሰወረውን የመግለጥ ልዩ ችሎታም ነበረው። ስለዚህ ዳንኤልን አስጠራ፤ እርሱም የጽሕፈቱን ትርጕም ይነግርሃል።”