ከዚያም ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል ለጥቂት ጊዜ በጣም ታወከ፤ ሐሳቡም አስደነገጠው። ንጉሡም፣ “ብልጣሶር ሆይ፤ ሕልሙም ሆነ ትርጕሙ አያስደንግጥህ” አለው። ብልጣሶርም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ሕልሙ ለሚጠሉህ ይሁን፤ ትርጕሙም ለጠላቶችህ! እጅግ አድጎና ጠንክሮ ያየኸው ዛፍ፣ ጫፉም እስከ ሰማይ ደርሶ በምድር ሁሉ የሚታየው፣ ቅጠሎቹ የሚያምሩ፣ ፍሬውም ተንዠርግጎ ለሁሉ ምግብ የሆነው፣ የዱር አራዊት መጠለያ የሆነውና በቅርንጫፎቹ ላይ ለሰማይ ወፎች ጐጆ መሥሪያ ያለው፣ ንጉሥ ሆይ፤ ያ ዛፍ አንተ ነህ! ታላቅና ብርቱ ሆንህ፤ ታላቅነትህ አድጎ እስከ ሰማይ ደረሰ፤ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ተንሰራፋ። “ንጉሥ ሆይ፤ አንተ፣ ‘ዛፉን ቍረጡ፣ አጥፉትም፤ በብረትና በናስ የታሰረውን ጕቶና ሥሩን በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ፤ በሰማይ ጠል ይረስርስ፤ እንደ ዱር አራዊትም ይኑር፤ ሰባት ዓመትም ይለፍበት’ እያለ ከሰማይ የወረደውን ቅዱሱን መልእክተኛ አየህ። “ንጉሥ ሆይ፤ ትርጕሙ ይህ ነው፤ ልዑሉ በንጉሡ በጌታዬ ላይ ያወጣው ዐዋጅ ይህ ነው፤ ከሕዝብ ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ ዱር አራዊትም ጋራ ትኖራለህ። እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ በሰማይ ጠልም ትረሰርሳለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመታት ያልፉብሃል። የዛፉ ጕቶ ከነሥሩ እንዲቀር መታዘዙ፣ ሥልጣን ከሰማይ መሆኑን ስታውቅ መንግሥትህ እንደሚመለስልህ ያመለክታል። ስለዚህ ንጉሥ ሆይ፤ ምክሬን ስማ፤ ኀጢአት መሥራትን ትተህ ትክክለኛ የሆነውን አድርግ፤ ክፋትን ትተህ ለተጨቈኑት ቸርነትን አድርግ፤ ምናልባት በሰላም የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል።” ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ከዐሥራ ሁለት ወራት በኋላ፣ ንጉሡ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ሲመላለስ ሳለ፣ “በብርቱ ኀይሌ፣ ለገናናው ክብሬ ንጉሣዊ መኖሪያ ትሆን ዘንድ ያሠራኋት ታላቂቷ ባቢሎን ይህች አይደለችምን?” አለ። ንግግሩን ገና ከአፉ ሳይጨርስ፣ እንዲህ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ “ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ፤ ስለ አንተ የታወጀው ይህ ነው፤ መንግሥትህ ከአንተ ተወስዷል፤ ከሕዝብ መካከል ትሰደዳለህ፤ ከዱር አራዊት ጋራም ትኖራለህ፤ እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለውና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመት ያልፋል።” ወዲያውኑ በናቡከደነፆር ላይ የተነገረው ሁሉ ተፈጸመ፤ ከሕዝቡ መካከል ተሰደደ፤ እንደ ከብትም ሣር በላ። የራስ ጠጕሩ እንደ ንስር ላባና፣ ጥፍሮቹም እንደ ወፍ ጥፍሮች እስኪያድጉ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ።
ዳንኤል 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ዳንኤል 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዳንኤል 4:19-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች