ዳንኤል 3:13-27

ዳንኤል 3:13-27 NASV

ንጉሥ ናቡከደነፆር በታላቅ ቍጣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስጠራቸው፤ እነዚህንም ሰዎች በንጉሡ ፊት አቀረቧቸው፤ ናቡከደነፆርም እንዲህ አላቸው፤ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ፤ እኔ ላቆምሁት ምስል አለመስገዳችሁ፣ አማልክቴንም አለማገልገላችሁ እውነት ነው? አሁንም ቢሆን የመለከቱንና የእንቢልታውን፣ የመሰንቆውንና የክራሩን፣ የበገናውንና የዋሽንቱን፣ የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ እኔ ላቆምሁት የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ ለመስገድ ዝግጁ ከሆናችሁ መልካም! ባትሰግዱለት ግን ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ታዲያ ከእጄ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?” ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ በዚህ ጕዳይ ላይ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት አያስፈልገንም። ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል። ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።” ከዚያም ናቡከደነፆር በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ እጅግ ተቈጣ፣ ፊቱም ተለወጠባቸው፤ የእቶኑ እሳትም ቀደም ሲል ከነበረው ሰባት ዕጥፍ ተደርጎ እንዲነድድ አዘዘ። ከሰራዊቱም ብርቱ የሆኑትን ጥቂት ወታደሮች፣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ። እነርሱም መጐናጸፊያቸውን፣ ሱሪያቸውን፣ የራስ ጥምጥማቸውንና ሌሎች ልብሶቻቸውን እንደ ለበሱ ታስረው በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ። የንጉሡ ትእዛዝ አስቸኳይ ስለ ነበረና የእቶኑም እሳት እጅግ ስለ ነደደ፣ የእሳቱ ወላፈን ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን ወስደው የጣሏቸውን ወታደሮች ገደላቸው። ሦስቱ ሰዎች ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ግን ተጠፍረው እንደ ታሰሩ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ወደቁ። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ናቡከደነፆር በአድናቆት ከተቀመጠበት ዘልሎ በመነሣት አማካሪዎቹን “አስረን በእሳት ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት አልነበሩምን?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ንጉሥ ሆይ፤ እውነት ነው” አሉ። እርሱም፣ “እነሆ፤ ያልታሰሩና ያልተጐዱ አራት ሰዎች በእሳቱ ውስጥ ሲመላለሱ አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል” አላቸው። ናቡከደነፆርም ወደሚነድደው የእቶን እሳት በር ቀረብ ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ፣ “እናንተ የልዑል አምላክ አገልጋዮች ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ፤ ኑ ውጡ! ወደዚህ ኑ!” አላቸው። ስለዚህ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ ከእሳቱ ወጡ፤ መኳንንቱ፣ ሹማምቱ፣ አገረ ገዦቹና የቤተ መንግሥት አማካሪዎችም በዙሪያቸው ተሰበሰቡ፤ እነርሱም እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጐዳ፣ ከራሳቸውም ጠጕር አንዲቷ እንኳ እንዳልተቃጠለች አዩ፤ የመጐናጸፊያቸው መልክ አልተለወጠም፤ የእሳትም ሽታ በላያቸው አልነበረም።