ዳንኤል 2:24-30

ዳንኤል 2:24-30 NASV

ዳንኤልም የባቢሎንን ጠቢባን እንዲገድል ንጉሡ ወዳዘዘው ወደ አርዮክ ሄዶ፣ “የባቢሎንን ጠቢባን አትግደል፤ ወደ ንጉሡ ውሰደኝ፤ እኔም ሕልሙን እተረጕምለታለሁ” አለው። አርዮክም ዳንኤልን ወዲያውኑ ወደ ንጉሡ በመውሰድ፣ “ሕልሙንና ትርጕሙን ለንጉሡ መግለጥ የሚችል ሰው ከይሁዳ ምርኮኞች መካከል አግኝቻለሁ” አለው። ንጉሡም ብልጣሶር የተባለውን ዳንኤልን፣ “ያየሁትን ሕልምና ትርጕሙን ልትነግረኝ ትችላለህን?” አለው። ዳንኤልም እንዲህ አለ፤ “አንድም ጠቢብ፣ አስማተኛ፣ ጠንቋይም ሆነ ቃላተኛ ንጉሡ የጠየቀውን ምስጢር መግለጥ የሚችል የለም፤ ነገር ግን ምስጢርን የሚገልጥ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱም በሚመጡት ዘመናት የሚሆነውን ነገር ለንጉሥ ናቡከደነፆር ገልጧል፤ በዐልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ በአእምሮህ የነበረው ሕልምና ራእይ ይህ ነው፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ተኝተህ ሳለ፣ አእምሮህ ወደ ፊት ሊሆን ስላለው ነገር ያሰላስል ነበር፤ ምስጢርን ገላጭ የሆነውም ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር አሳየህ። ይህ ምስጢር ለእኔ የተገለጠው፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ ታላቅ ጥበብ ስላለኝ አይደለም፤ ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ትርጕሙን እንድታውቅና በአእምሮህ ታሰላስለው የነበረው ነገር ምን እንደ ሆነ ትረዳ ዘንድ ነው።