ዳንኤል 12:5-13

ዳንኤል 12:5-13 NASV

እኔም ዳንኤል ተመለከትሁ፤ እነሆ ከፊት ለፊቴ ሌሎች ሁለት ቆመው ነበር፤ አንዱ ከወንዙ በዚህኛው ዳር፣ ሌላው ደግሞ ከወንዙ በዚያኛው ዳር። ከእነርሱም አንዱ፣ ከወንዙ ውሃ በላይ የነበረውንና በፍታ የለበሰውን ሰው፣ “እነዚህ አስደናቂ ነገሮች ሊፈጸሙ ምን ያህል ጊዜ ይቀራል?” አለው። ከወንዙ ውሃ በላይ የነበረው በፍታ የለበሰው ሰው፣ ቀኝ እጁንና ግራ እጁን ወደ ሰማይ አንሥቶ፣ “ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመንም እኩሌታ ይሆናል፤ የተቀደሰው ሕዝብ ኀይል መሰበር ሲያከትም፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ይፈጸማሉ” ብሎ ለዘላለም በሚኖረው በርሱ ሲምል ሰማሁ። እኔም ሰማሁ፤ ነገር ግን አላስተዋልሁትም፤ ስለዚህ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ የዚህ ሁሉ ፍጻሜ ምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ዳንኤል ሆይ፤ ቃሉ እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ስለ ሆነ ሂድ። ብዙዎች ይነጻሉ፤ ይጠራሉ፤ እንከን አልባም ይሆናሉ፤ ክፉዎች ግን በክፋታቸው ይጸናሉ፤ ከክፉዎች አንዳቸውም አያስተውሉም፤ ጠቢባን ግን ያስተውላሉ። “የዘወትሩ መሥዋዕት ከተቋረጠበትና ጥፋትን የሚያመጣው የጥፋት ርኩሰት ከተተከለበት ጊዜ ጀምሮ አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ዘጠና ቀን ይሆናል። የሚታገሥና እስከ አንድ ሺሕ ሦስት መቶ ሠላሳ ዐምስት ቀን ፍጻሜ የሚደርስ ብፁዕ ነው። “አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ፤ ታርፋለህ፤ በቀኖቹ መጨረሻም ተነሥተህ የተመደበልህን ርስት ትቀበላለህ።”