እንግዲህ ከክርስቶስ ጋራ ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን ፈልጉ፤ ሐሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን። ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋራ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሯልና፤ ሕይወታችሁ የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም በዚያ ጊዜ ከርሱ ጋራ በክብር ትገለጣላችሁ። ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም፦ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው። በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙት ላይ ይመጣል፤ እናንተም ቀድሞ በኖራችሁበት ሕይወት በእነዚህ ትመላለሱ ነበር፤ አሁን ግን ቍጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትን፣ ስድብንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋራ አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁም ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሠኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት። እንደ አንድ አካል ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። በርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። ሚስቶች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ ተገቢ በመሆኑ ለባሎቻችሁ ተገዙ። ባሎች ሆይ፤ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው። ልጆች ሆይ፤ ይህ ጌታን ደስ የሚያሰኝ በመሆኑ በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ። አባቶች ሆይ፤ ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው። ባሮች ሆይ፤ ለታይታ ሰውን እንደሚያስደስቱት ሳይሆን፣ በቅን ልብ ጌታን በመፍራት ለምድራዊ ጌቶቻችሁ በሁሉ ነገር ታዘዙ። የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት፤ ከጌታ ዘንድ እንደ ብድራት የምትቀበሉት ርስት እንዳለ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው። በደለኛውም የእጁን ያገኛል፤ አድልዎም የለም።
ቈላስይስ 3 ያንብቡ
ያዳምጡ ቈላስይስ 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ቈላስይስ 3:1-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች