ቈላስይስ 3:1-15

ቈላስይስ 3:1-15 NASV

እንግዲህ ከክርስቶስ ጋራ ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን ፈልጉ፤ ሐሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን። ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋራ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሯልና፤ ሕይወታችሁ የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም በዚያ ጊዜ ከርሱ ጋራ በክብር ትገለጣላችሁ። ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም፦ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው። በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙት ላይ ይመጣል፤ እናንተም ቀድሞ በኖራችሁበት ሕይወት በእነዚህ ትመላለሱ ነበር፤ አሁን ግን ቍጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትን፣ ስድብንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋራ አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁም ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሠኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት። እንደ አንድ አካል ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ።