አሞጽ 2:6-16

አሞጽ 2:6-16 NASV

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የእስራኤል ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ጻድቁን ስለ ጥሬ ብር፣ ድኻውንም ስለ ጥንድ ጫማ ይሸጡታልና። የችግረኞችን ራስ፣ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፤ ፍትሕንም ከጭቍኖች ይነጥቃሉ፤ አባትና ልጅ ከአንዲት ሴት ጋራ ይተኛሉ፤ እንዲህም እያደረጉ ቅዱስ ስሜን ያረክሳሉ። በመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ፣ በየመሠዊያው ሥር ይተኛሉ፤ በአምላካቸው ቤት፣ በመቀጫነት የተወሰደውን የወይን ጠጅ ይጠጣሉ። “ቁመቱ እንደ ዝግባ፣ ጥንካሬውም እንደ ወርካ ዛፍ የነበረ ቢሆንም፣ አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁት፣ ከላይ ፍሬውን፣ ከታችም ሥሩን አጠፋሁ። የአሞራውያንን ምድር ልሰጣችሁ፣ ከግብጽ አወጣኋችሁ፤ አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መራኋችሁ። “ደግሞም ነቢያትን ከወንዶች ልጆቻችሁ መካከል፣ ናዝራውያንንም ከጕልማሶቻችሁ መካከል አስነሣሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ ይህ እውነት አይደለምን?” ይላል እግዚአብሔር። “እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤ ነቢያቱንም ትንቢት እንዳይናገሩ አዘዛችኋቸው። “እነሆ፤ በእህል የተሞላ ጋሪ እንደሚያደቅቅ፣ እኔም አደቅቃችኋለሁ። ፈጣኑ አያመልጥም፤ ብርቱውንም ብርታቱ አይረዳውም፤ ኀያሉም ነፍሱን አያድንም። ቀስተኛው በቦታው ጸንቶ አይቆምም፤ ፈጣኑም ተዋጊ ሮጦ አያመልጥም፤ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም። ጐበዞቹ ተዋጊዎች እንኳ፣ በዚያ ቀን ዕራቍታቸውን ይሸሻሉ፤” ይላል እግዚአብሔር።