ሐዋርያት ሥራ 9:23-30

ሐዋርያት ሥራ 9:23-30 NASV

ከብዙ ቀንም በኋላ፣ አይሁድ ሳውልን ለመግደል አሤሩ፤ ሳውል ግን ዕቅዳቸውን ዐውቆ ነበር፤ እነርሱም ሊገድሉት የከተማዋን በር ቀንና ሌሊት ይጠብቁ ነበር፤ የርሱ ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት በከተማዪቱ ቅጥር ቀዳዳ አሹልከው በቅርጫት አወረዱት። ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርት ጋራ ለመቀላቀል ሞከረ፤ እነርሱ ግን በርግጥ ደቀ መዝሙር መሆኑን ስላላመኑ ሁሉም ፈሩት። ይሁን እንጂ በርናባስ ወስዶ ወደ ሐዋርያት አመጣው፤ ሳውልም በጕዞው ላይ ሳለ ጌታን እንዴት እንዳየው፣ ጌታም እንዴት እንደ ተናገረው እንዲሁም በደማስቆ በኢየሱስ ስም እንዴት በድፍረት እንደ ሰበከ ነገራቸው። ስለዚህ ሳውል ዐብሯቸው ተቀመጠ፤ በኢየሩሳሌምም በመዘዋወር በጌታ ስም በድፍረት ይናገር ነበር። ከግሪክ አገር ከመጡት አይሁድ ጋራ እየተነጋገረ ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ጥረት ያደርጉ ነበር። ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ፣ ወደ ቂሳርያ አውርደው ወደ ጠርሴስ ሰደዱት።