ሐዋርያት ሥራ 9:1-19

ሐዋርያት ሥራ 9:1-19 NASV

ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል አሁንም እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ፤ የጌታን መንገድ የሚከተሉትን ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን በዚያ ካገኘ አስሮ ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ እንዲችል፣ በደማስቆ ለነበሩት ምኵራቦች ደብዳቤ እንዲሰጠው ሊቀ ካህናቱን ለመነው። ደማስቆ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው፣ ብርሃን ከሰማይ ድንገት በዙሪያው አንጸባረቀበት፤ እርሱም በመሬት ላይ ወደቀ፤ በዚያ ጊዜም “ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ። ሳውልም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?” አለው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “እኔማ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። ነገር ግን ተነሣና ወደ ከተማዪቱ ግባ፤ ማድረግ የሚገባህም ይነገርሃል።” ከሳውል ጋራ ይጓዙ የነበሩትም ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንንም ባላዩ ጊዜ፣ አፋቸውን ይዘው ቆሙ። ሳውልም ከመሬት ላይ ተነሥቶ ዐይኑን ሲገልጥ ምንም ማየት አልቻለም፤ ስለዚህ ሰዎቹ እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አስገቡት። ሦስት ቀንም ታወረ፤ እህል ውሃም አልቀመሰም። በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታም በራእይ፣ “ሐናንያ!” ብሎ ጠራው። እርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆኝ” አለ። ጌታም እንዲህ አለው፤ “ተነሣና ‘ቀጥተኛ ጐዳና’ በተባለው መንገድ ይሁዳ ወደ ተባለ ሰው ቤት ሂድ፤ እዚያም ሳውል የሚባል አንድ የጠርሴስ ሰው እየጸለየ ነውና ፈልገው፤ እርሱም ሐናንያ የሚባል ሰው እርሱ ወዳለበት መጥቶ እጁን እንደሚጭንበትና ዐይኑ እንደሚበራለት በራእይ አይቷል።” ሐናንያም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ይህ ሰው እኮ በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳንህ ላይ ምን ያህል ጕዳት እንዳደረሰ ከብዙ ሰው ሰምቻለሁ፤ ወደዚህም የመጣው ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብሎ ነው።” ጌታም እንዲህ አለው፤ “ሂድ! ይህ ሰው በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ስሜን እንዲሸከም የተመረጠ ዕቃዬ ነው፤ እኔም ስለ ስሜ ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት አሳየዋለሁ።” ሐናንያ ሄዶ፣ ወደተባለውም ቤት ገባ፤ በሳውልም ላይ እጁን ጭኖ፣ “ወንድሜ ሳውል ሆይ፤ ወደዚህ ስትመጣ በመንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ፣ ዐይንህ እንዲበራና በመንፈስ ቅዱስም እንድትሞላ እኔን ልኮኛል” አለው። ወዲያውም ከሳውል ዐይን ላይ ቅርፊት የመሰለ ነገር ወደቀ፤ እንደ ገና ማየት ቻለ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤ ምግብም በልቶ በረታ።