ሐዋርያት ሥራ 7:44-53

ሐዋርያት ሥራ 7:44-53 NASV

“እግዚአብሔር ለሙሴ ባሳየው ንድፍና ባዘዘው መሠረት የተሠራችው የምስክር ድንኳን፣ ከአባቶቻችን ጋራ በምድረ በዳ ነበረች። አባቶቻችንም ድንኳኗን ከተቀበሉ በኋላ፣ እግዚአብሔር በኢያሱ መሪነት ያሳደዳቸውን የአሕዛብን አገር በወረሱ ጊዜ ይዘዋት ገቡ፤ እስከ ዳዊትም ዘመን ድረስ በምድሪቱ ተቀመጠች፤ ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ በማግኘቱ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ ያዘጋጅ ዘንድ ለመነ፤ ነገር ግን የማደሪያውን ቤት የሠራለት ሰሎሞን ነበር። “ይሁን እንጂ፣ ልዑል የሰው እጅ በሠራው ቤት ውስጥ አይኖርም፤ ይህም ነቢዩ እንዲህ ባለው መሠረት ነው፤ “ ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ ማሳረፊያ ናት፤ ታዲያ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ? ይላል ጌታ፤ ወይስ ማረፊያ የሚሆነኝ ቦታ የት ነው? እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን?’ “እናንተ ልባችሁና ጆሯችሁ ያልተገረዘ! ዐንገተ ደንዳኖች ልክ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ሁልጊዜ ትቃወማላችሁ። ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን እንኳ ገድለዋል፤ እናንተም አሁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ገደላችሁትም፤ በመላእክት አማካይነት የተሰጣችሁንም ሕግ ተቀበላችሁ እንጂ አልጠበቃችሁትም።”