ሐዋርያት ሥራ 7:37-43

ሐዋርያት ሥራ 7:37-43 NASV

“የእስራኤልንም ልጆች፣ ‘እግዚአብሔር እንደ እኔ ያለ ነቢይ ከወንድሞቻችሁ መካከል ያስነሣላችኋል’ ያላቸው ይኸው ሙሴ ነበር። እርሱም በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋራ በምድረ በዳ በሕዝቡ ጉባኤ መካከል ነበር፤ የሕይወትንም ቃል ወደ እኛ ለማስተላለፍ ተቀበለ። “አባቶቻችን ግን ተቃወሙት እንጂ ሊታዘዙት ስላልፈለጉ በልባቸው ወደ ግብጽ ተመለሱ። አሮንንም፣ ‘በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅምና!’ አሉት። በዚያ ጊዜ የጥጃ ምስል ሠርተው፣ ለጣዖቱ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ተደሰቱ፤ ፈነጠዙም። እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ ዘወር አለ፤ ያመልኳቸውም ዘንድ ለሰማይ ከዋክብት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም በነቢያት መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት ተፈጸመ፤ “ ‘እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አርባ ዓመት በምድረ በዳ፣ መሥዋዕትንና ቍርባንን አቅርባችሁልኝ ነበርን? ይልቁንም ልታመልኳቸው የሠራችኋቸውን፣ የሞሎክን ድንኳንና የኮከብ አምላክ የሆነውን የሬምፋም ጣዖት አንሥታችሁ ተሸከማችሁ። ስለዚህ ከባቢሎን ማዶ እንድትጋዙ አደርጋለሁ።’