ሐዋርያት ሥራ 7:30-36

ሐዋርያት ሥራ 7:30-36 NASV

“ከአርባ ዓመት በኋላ፣ በሲና ተራራ አካባቢ ባለው ምድረ በዳ፣ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መልአክ ተገለጠለት። ሙሴም ባየው ነገር ተደነቀ፤ ነገሩን ለማጣራት ወደዚያ ሲቀርብ የጌታ ድምፅ፤ ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይሥሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ሲል ሰማ። ሙሴም በፍርሀት ተዋጠ፤ ለመመልከትም አልደፈረም። “ጌታም እንዲህ አለው፤ ‘የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማውን ከእግርህ አውልቅ፤ በግብጽ ያለውን የሕዝቤን መከራ በርግጥ አይቻለሁ፤ የጭንቅ ጩኸታቸውን ሰምቻለሁ፤ ላድናቸውም ወርጃለሁ። አሁንም ና፤ ወደ ግብጽ መልሼ እልክሃለሁ።’ “እንግዲህ እነዚያ፣ ‘አንተን ገዥና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው?’ ብለው የናቁትን ይህን ሙሴ እግዚአብሔር በቍጥቋጦው ውስጥ በታየው መልአክ አማካይነት ገዥና ታዳጊ አድርጎ ወደ እነርሱ ላከው። እርሱም መርቶ ከግብጽ አወጣቸው፤ በግብጽ፣ በቀይ ባሕርና በምድረ በዳ አርባ ዓመት ድንቅ ነገሮችንና ታምራዊ ምልክቶችን አደረገ።