ሐዋርያት ሥራ 7:1-8

ሐዋርያት ሥራ 7:1-8 NASV

ሊቀ ካህናቱም፣ “ይህ የቀረበብህ ክስ እውነት ነውን?” አለው። እስጢፋኖስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፤ አድምጡኝ! አባታችን አብርሃም ወደ ካራን ከመምጣቱ በፊት፣ ገና በመስጴጦምያ ሳለ፣ የክብር አምላክ ተገልጦለት፣ ‘ከአገርህና ከወገንህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ’ አለው። “እርሱም ከከለዳውያን ምድር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከአባቱም ሞት በኋላ፣ አሁን እናንተ ወደምትኖሩበት ወደዚህ አገር አመጣው። በዚህም ስፍራ አንዲት ጫማ ታኽል እንኳ ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን በዚያ ጊዜ ምንም ልጅ ሳይኖረው፣ እርሱና ከርሱም በኋላ ዘሩ ምድሪቱን እንደሚወርሱ እግዚአብሔር ቃል ገባለት። ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ‘ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ ይሆናል፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል። ነገር ግን በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እኔ ደግሞ እቀጣዋለሁ፤’ ደግሞም ‘ከዚያም አገር ወጥተው በዚህ ስፍራ ያመልኩኛል።’ ይላል እግዚአብሔር። ከዚያም የግዝረትን ኪዳን ሰጠው፤ አብርሃምም ይሥሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው። ይሥሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን የነገድ አባቶች ወለደ።