ሐናንያ የተባለ ሰው፣ ከሚስቱ ከሰጲራ ጋራ መሬት ሸጠ፤ ሚስቱም በሚገባ እያወቀች ከሽያጩ የተወሰነ ገንዘብ በማስቀረት፣ የተረፈውን አምጥቶ በሐዋርያት እግር ሥር አስቀመጠ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለ፤ “ሐናንያ ሆይ፤ መንፈስ ቅዱስን ትዋሽና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን ልብህን ለምን ሞላው? ሳትሸጠው በፊት የአንተው አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ ቢሆን ገንዘቡ በእጅህ አልነበረምን? ለመሆኑ ይህን ነገር እንዴት በልብህ አሰብህ? የዋሸኸው እኮ እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም።” ሐናንያም ይህን እንደ ሰማ ወድቆ ሞተ፤ ይህን የሰሙትም ሁሉ ታላቅ ፍርሀት ያዛቸው። ጕልማሶችም ተነሥተው አስከሬኑን ገነዙት፤ ወስደውም ቀበሩት። ሦስት ሰዓት ያህልም ካለፈ በኋላ፣ ሚስቱ የሆነውን ሳታውቅ መጥታ ገባች። ጴጥሮስም፣ “እስኪ ንገሪኝ፤ መሬታችሁን የሸጣችሁት በዚህ ዋጋ ነውን?” አላት። እርሷም፣ “አዎን፤ በዚሁ ዋጋ ነው” አለች። ጴጥሮስም፣ “የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ እንዴት እንዲህ ተስማማችሁ? እነሆ፤ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች ተመልሰው እግራቸው ደጃፍ ላይ ነው! አንቺንም ይዘው ይወጣሉ” አላት። እርሷም ወዲያውኑ እግሩ ሥር ወድቃ ሞተች፤ ጕልማሶቹም ሲገቡ ሞታ አገኟት፤ አውጥተውም በባሏ አጠገብ ቀበሯት። መላዪቱን ቤተ ክርስቲያንና ይህን የሰሙትን ሁሉ ታላቅ ፍርሀት ያዛቸው። ሐዋርያትም በሕዝቡ መካከል ብዙ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ሥራዎችን አደረጉ፤ አማኞቹም ሁሉ “የሰሎሞን ደጅ” በተባለው መመላለሻ ይሰበሰቡ ነበር። ከእነርሱ ጋራ ሊቀላቀል የደፈረ ማንም አልነበረም፤ ሆኖም ሕዝቡ እጅግ ያከብሯቸው ነበር፤ ብዙ ወንዶችና ሴቶችም ከጊዜ ወደ ጊዜ በጌታ እያመኑ ወደ እነርሱ ይጨመሩ ነበር። ከዚህም የተነሣ፣ ጴጥሮስ በዚያ ሲያልፍ፣ ቢያንስ ጥላው እንኳ በጥቂቶች ላይ እንዲያርፍባቸው በማለት ሕመምተኞችን ወደ ውጭ እያወጡ በዐልጋና በቃሬዛ በመንገድ ላይ ያስተኙ ነበር። በኢየሩሳሌም አካባቢ ከሚገኙ ከተሞች፣ ሕመምተኞችንና በርኩሳን መናፍስት የሚሠቃዩትን ይዘው የሚመጡት ሰዎች አካባቢውን ያጨናንቁት ነበር፤ የመጡትም ሁሉ ይፈወሱ ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 5
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 5:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች