ሐዋርያት ሥራ 4:22-31

ሐዋርያት ሥራ 4:22-31 NASV

በዚህ ታምር የተፈወሰውም ሰው ዕድሜው ከአርባ ዓመት በላይ ነበርና። ጴጥሮስና ዮሐንስም ከተፈቱ በኋላ ወደ ወገኖቻቸው ተመልሰው፣ የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሏቸውን ሁሉ ነገሯቸው። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ድምፃቸውን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “ልዑል ጌታ ሆይ፤ አንተ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል፤ በመንፈስ ቅዱስም አማካይነት በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለህ ተናግረሃል፤ “ ‘አሕዛብ ለምን በቍጣ ተነሣሡ? ሕዝቡስ ለምን በከንቱ አሤሩ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ ገዦችም በጌታና በመሲሑ ላይ ሊመክሩ ተሰበሰቡ።’ በእውነትም ሄሮድስና ጳንጥዮስ ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋራ በዚህች ከተማ አንተ በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ለማሤር ተሰበሰቡ፤ ይህም የሆነው የአንተ ክንድና ፈቃድ ጥንት የወሰኑት እንዲፈጸም ነው። አሁንም ጌታ ሆይ፤ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሮችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገር እንዲችሉ አድርጋቸው። ለመፈወስ እጅህን ዘርጋ፤ በቅዱሱ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ድንቅና ታምራት አድርግ።” ከጸለዩም በኋላ የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በድፍረት ተናገሩ።