ሰዎቹም፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ እንዲህ በድፍረት ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ፣ ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ፤ ከኢየሱስ ጋራ እንደ ነበሩም ተገነዘቡ። የተፈወሰውን ሰው እዚያው ከእነርሱ ጋራ ቆሞ ስላዩት የሚናገሩበትን ሰበብ ዐጡ። ስለዚህ ከሸንጎው እንዲያወጧቸው አዘዙ፤ ከዚያም በአንድነት ተሰብስበው ተመካከሩ፤ እንዲህም ተባባሉ፤ “እንግዲህ እነዚህን ሰዎች ምን እናድርጋቸው? በኢየሩሳሌም የሚኖር ሁሉ በእነርሱ እጅ የተደረገውን ድንቅ ታምር ዐውቋል፣ ስለዚህ ይህን ማስተባበል አንችልም፤ ይሁን እንጂ፣ ይህ ነገር ከእንግዲህ በሕዝቡ መካከል ይበልጥ እንዳይስፋፋ፣ እነዚህም ሰዎች ዳግመኛ በዚህ ስም ለማንም እንዳይናገሩ እናስጠንቅቃቸው።” ከጠሯቸውም በኋላ፣ በኢየሱስ ስም ፈጽሞ እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዟቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው እንዲህ አሏቸው፤ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ይገባ እንደ ሆነ እስኪ እናንተው ፍረዱ! እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም።” እንደ ገና ከዛቱባቸው በኋላም ለቀቋቸው፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ስለ ነበር ሊቀጧቸው አልቻሉም፤ በዚህ ታምር የተፈወሰውም ሰው ዕድሜው ከአርባ ዓመት በላይ ነበርና። ጴጥሮስና ዮሐንስም ከተፈቱ በኋላ ወደ ወገኖቻቸው ተመልሰው፣ የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሏቸውን ሁሉ ነገሯቸው። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ድምፃቸውን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “ልዑል ጌታ ሆይ፤ አንተ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል፤ በመንፈስ ቅዱስም አማካይነት በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለህ ተናግረሃል፤ “ ‘አሕዛብ ለምን በቍጣ ተነሣሡ? ሕዝቡስ ለምን በከንቱ አሤሩ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ ገዦችም በጌታና በመሲሑ ላይ ሊመክሩ ተሰበሰቡ።’ በእውነትም ሄሮድስና ጳንጥዮስ ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋራ በዚህች ከተማ አንተ በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ለማሤር ተሰበሰቡ፤ ይህም የሆነው የአንተ ክንድና ፈቃድ ጥንት የወሰኑት እንዲፈጸም ነው። አሁንም ጌታ ሆይ፤ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሮችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገር እንዲችሉ አድርጋቸው። ለመፈወስ እጅህን ዘርጋ፤ በቅዱሱ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ድንቅና ታምራት አድርግ።” ከጸለዩም በኋላ የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በድፍረት ተናገሩ። ያመኑትም ሁሉ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ነበር፤ ያላቸውም ሁሉ የጋራ ነበር እንጂ የራሱ የሆነውን ሀብት እንኳ እንደ ግሉ የሚቈጥር ማንም አልነበረም። ሐዋርያትም ስለ ጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ በታላቅ ኀይል መመስከራቸውን ቀጠሉ፤ በሁላቸውም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበር። ከመካከላቸውም አንድ ችግረኛ አልነበረም፤ ምክንያቱም መሬትም ሆነ ቤት የነበራቸውን ሁሉ እየሸጡ ዋጋውን አምጥተው፣ በሐዋርያት እግር ሥር በማስቀመጥ ለእያንዳንዱ በሚያስፈልገው መጠን ያካፍሉት ነበር። በቆጵሮስ የሚኖር ዮሴፍ የሚባል አንድ ሌዋዊ ነበረ፤ ሐዋርያትም “በርናባስ” ብለው ጠሩት፤ ትርጕሙም “የመጽናናት ልጅ” ማለት ነው፤ እርሱም መሬቱን ሸጦ፣ ገንዘቡን አምጥቶ በሐዋርያት እግር ሥር አስቀመጠ።
ሐዋርያት ሥራ 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 4:13-37
8 ቀናት
ክርስቲያን ከሆንክ ያለማቋረጥ በጦርነት ላይ ነህ። በአካላዊ ጉዳት ስለተጠቃህ አይደለም፣ ነገር ግን መንፈሳዊ ኃይሎች ከአምላክ ሊያርቁህ ስለሚሞክሩ ነው። አንተን ለመጠበቅ እግዚአብሔር መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ይሰጥሃል። ይህ የንባብ እቅድ - የእግዚአብሔር የጦር ትጥቅ ምን እንደሚመስል እና እንዴት እንደሚጠቀሙበት ያብራራል።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች