ሐዋርያት ሥራ 21:1-23

ሐዋርያት ሥራ 21:1-23 NASV

ከእነርሱ ከተለየን በኋላ ቀጥታ በመርከብ ወደ ቆስ ተጓዝን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ፣ ከዚያም ወደ ጳጥራ አመራን። በዚያም ወደ ፊንቄ የሚሄድ መርከብ ስላገኘን፣ ተሳፍረን ጕዟችንን ቀጠልን። ቆጵሮስ በታየችን ጊዜ፣ ወደ ግራ ትተናት ዐለፍንና ወደ ሶርያ አመራን፤ መርከባችን ጭነቱን በጢሮስ ማራገፍ ስለ ነበረበት እኛም እዚያው ወረድን። ደቀ መዛሙርትንም በዚያ አግኝተን፣ ሰባት ቀን ከእነርሱ ጋራ ተቀመጥን። እነርሱም በመንፈስ ሆነው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ነገሩት። የቈይታ ጊዜያችን ባለቀ ጊዜ፣ ትተናቸው ጕዟችንን ቀጠልን፤ ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋራ እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ ከተሰነባበትንም በኋላ እኛ ወደ መርከቡ ገባን፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ከጢሮስ ተነሥተን ጕዟችንን በመቀጠል ጴጤሌማይስ ደረስን፤ ከመርከብ ወርደንም ለወንድሞች ሰላምታ ካቀረብን በኋላ፣ አንድ ቀን ከእነርሱ ጋራ ቈየን። በማግስቱም ከዚያ ተነሥተን ቂሳርያ ደረስን፤ ከሰባቱ ወንጌላውያን አንዱ በሆነው በፊልጶስ ቤትም ዐረፍን። እርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጥን በኋላ አጋቦስ የተባለ ነቢይ ከይሁዳ ወረደ፤ ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወሰደ፤ የራሱንም እጅና እግር በማሰር፣ “መንፈስ ቅዱስ፣ ‘በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት እንዲህ አድርገው በማሰር ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል’ ይላል” አለ። ይህን ስንሰማ እኛና በዚያም የሚኖሩት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመንነው። ጳውሎስ ግን፣ “ለምን እንዲህ እያለቀሳችሁ ልቤን ታባቡታላችሁ? እኔ መታሰር ቀርቶ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ዝግጁ ነኝ” አላቸው። ምክራችንን አልቀበል ስላለን፣ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው። ከዚህ በኋላ፣ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። በቂሳርያ ከነበሩት ደቀ መዛሙርትም አንዳንዶቹ ወደ ምናሶን ቤት ይዘውን መጡ፤ እኛም በዚያው ተቀመጥን። ምናሶን የቆጵሮስ ሰው ሲሆን፣ ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበረ። ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። በማግስቱም ጳውሎስና ሌሎቻችንም ያዕቆብን ለማየት ሄድን፤ ሽማግሌዎችም ሁሉ በዚያ ነበሩ። ጳውሎስም ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ፣ እግዚአብሔር በርሱ አገልግሎት አማካይነት በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ሁሉ በዝርዝር አስረዳቸው። እነርሱም ይህን ሲሰሙ፣ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ጳውሎስንም እንዲህ አሉት፤ “ወንድም ሆይ፤ በብዙ ሺሕ የሚቈጠሩ አይሁድ እንዳመኑ ተመልከት፤ ሁሉም ደግሞ ለሙሴ ሕግ የሚቀኑ ናቸው። በአሕዛብ መካከል የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ ሙሴን እንዲተዉና ልጆቻቸውን እንዳይገርዙ፣ በቈየው ልማዳችን መሠረት እንዳይኖሩ እንደምታስተምር ስለ አንተ ተነግሯቸዋል። መምጣትህን መስማታቸው የማይቀር ነውና እንግዲህ ምን እናድርግ? ስለዚህ የምንልህን አድርግ። ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ፤