ሐዋርያት ሥራ 2:14-28

ሐዋርያት ሥራ 2:14-28 NASV

በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋራ ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፤ “እናንተ የይሁዳ ሰዎች፤ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፤ ይህን አንድ ነገር ዕወቁ፤ በጥሞናም አድምጡ። ጊዜው ገና ከጧቱ ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ፣ እናንተ እንደምታስቡት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም! ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል እንዲህ ተብሎ የተነገረ ነው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመጨረሻው ቀን፣ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጕልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ። በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሮቼም ላይ፣ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ። በላይ በሰማያት ድንቅ ነገሮችን፣ አሳያለሁ፤ በታች በምድርም ምልክቶችን እሰጣለሁ፤ ደምና እሳት፣ የጢስም ዐምድ ይሆናል። ታላቁና ክቡር የሆነው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም፣ የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ይህን ቃል ስሙ፤ እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ታምራትን፣ ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል። እግዚአብሔር በጥንት ውሳኔውና በቀደመው ዕውቀቱ ይህን ሰው አሳልፎ በእጃችሁ ሰጣችሁ፤ እናንተም በክፉ ሰዎች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አስወግዶ አስነሣው፤ ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለምና። ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፤ “ ‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እርሱ በቀኜ ነውና፣ ከቶ አልታወክም። ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬም በተስፋ ይኖራል። ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ቅዱስህም መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም። የሕይወትን መንገድ እንዳውቅ አደረግኸኝ፤ በፊትህም በሐሤት ትሞላኛለህ።’