ጳውሎስ በአቴና ሆኖ ሲጠብቃቸው ሳለ፣ ከተማዪቱ በጣዖት የተሞላች መሆኗን በማየት መንፈሱ ተበሳጨበት። ስለዚህ በምኵራብ ሆኖ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ግሪኮች ጋራ፣ ደግሞም በገበያ ስፍራ ዕለት ዕለት ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋራ ይነጋገር ነበር። ከኤፊቆሮስና ከኢስጦኢክ የፍልስፍና ወገን የሆኑትም ወደ እርሱ መጥተው ይከራከሩት ነበር። አንዳንዶቹ፣ “ይህ ለፍላፊ ምን ለማለት ይፈልጋል?” ይሉ ነበር፤ ሌሎች ደግሞ ስለ ኢየሱስና ስለ ትንሣኤው የምሥራች ሲሰብክ ሰምተው፣ “ስለ አዳዲስ ባዕዳን አማልክት የሚናገር ይመስላል” አሉ። ይዘውም አርዮስፋጎስ ወደተባለው ስፍራ በመውሰድ እንዲህ አሉት፤ “አንተ የምታስተምረው ይህ አዲስ ትምህርት ምን እንደ ሆነ እንድናውቅ ትፈቅዳለህን? ደግሞም በጆሯችን የምታሰማን እንግዳ ነገር ስለ ሆነብን፣ ምን ማለት እንደ ሆነ ማወቅ እንፈልጋለን።” የአቴና ሰዎች በሙሉ እንዲሁም በዚያ የሚኖሩ የውጭ ሰዎች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስለ አዳዲስ ነገሮች በማውራትና በመስማት እንጂ በሌላ ጕዳይ አልነበረም። ስለዚህ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአቴና ሰዎች ሆይ! በማናቸውም ረገድ፣ በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን አያለሁ፤ እየተዘዋወርሁ ሳለሁ፣ የምታመልኳቸውን ነገሮች ስመለከት፣ ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሑፍ ያለበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁና፤ እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ። “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነው፤ ስለዚህም እርሱ የሰው እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም። እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም። የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን ፈጥሮ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ አደረገ፤ የዘመናቸውን ልክና የመኖሪያ ስፍራቸውንም ዳርቻ ወሰነላቸው። ይኸውም ሰዎች እግዚአብሔርን ፈልገው ተመራምረው ምናልባት ያገኙት እንደ ሆነ ብሎ ነው፤ ይህም ቢሆን እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ሆኖ አይደለም፤ የምንኖረውና የምንንቀሳቀሰው፣ ያለነውም በርሱ ነውና። ከራሳችሁ ባለቅኔዎችም አንዳንዶቹ እንዳሉት፣ ‘እኛም ደግሞ ልጆቹ ነን።’ “እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን፣ አምላክ በሰው ሙያና ጥበብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ ይመስላል ብለን ማሰብ አይገባንም። ቀደም ሲል እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን አለማወቅ በትዕግሥት ዐልፏል፤ አሁን ግን በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ ያዝዛል። በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኗልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጧል።” እነርሱም ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ፣ አንዳንዶቹ አፌዙ፤ ሌሎች ግን፣ “ስለዚህ ጕዳይ ከአንተ ዳግመኛ ለመስማት እንፈልጋለን” አሉት። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጥቶ ሄደ፤ አንዳንድ ሰዎች ግን ጳውሎስ ባለው በመስማማት ተከተሉት፤ አመኑም፤ ከእነዚህም ዲዮናስዮስ የተባለው የአርዮስፋጎስ ፍርድ ቤት አባል፣ ደማሪስ የተባለች ሴትና ሌሎችም ሰዎች ነበሩ።
ሐዋርያት ሥራ 17 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 17
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 17:16-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች