ሐዋርያት ሥራ 16:19-26

ሐዋርያት ሥራ 16:19-26 NASV

አሳዳሪዎቿም የገንዘብ ማግኛ ተስፋቸው ወጥቶ መሄዱን በተረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጐተቱ ባለሥልጣኖች ወዳሉበት ወደ ገበያ ቦታ አመጧቸው። ገዦቹም ፊት አቅርበዋቸው እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ሳሉ፣ ከተማችንን አውከዋል፤ ደግሞም እኛ ሮማውያን መቀበል ወይም መፈጸም ያልተፈቀደልንን ልማድ በሕዝቡ መካከል ይነዛሉ።” ሕዝቡም ተባብረው በጳውሎስና በሲላስ ላይ ተነሡባቸው፤ ገዦቹም ልብሳቸው ተገፍፎ በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ። ክፉኛ ከተደበደቡ በኋላም ወደ ወህኒ ቤት አስገቧቸው፤ የወህኒ ቤት ጠባቂውም ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም ይህን የመሰለ ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፣ ወደ ወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገብቶ እግራቸውን ከግንድ ጋራ አጣብቆ አሰራቸው። እኩለ ሌሊት አካባቢ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና እየዘመሩ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ነበር፤ ሌሎቹ እስረኞችም ያዳምጧቸው ነበር። ድንገትም የወህኒ ቤቱን መሠረት የሚያናውጥ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ፤ ወዲያውም የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፈቱ፤ የሁሉም እስራት ተፈታ።