አንድ ቀን ወደ ጸሎት ስፍራ ስንሄድ፣ በጥንቈላ መንፈስ ትንቢት የምትናገር አንዲት የቤት አገልጋይ አገኘችን፤ እርሷም በዚህ የጥንቈላ ሥራዋ ለአሳዳሪዎቿ ብዙ ገንዘብ ታስገኝላቸው ነበር። ይህችው አገልጋይ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፣ “እነዚህ ሰዎች የመዳንን መንገድ የሚነግሯችሁ፣ የልዑል እግዚአብሔር ባሮች ናቸው!” በማለት ትጮኽ ነበር፤ ይህንም ብዙ ቀን ደጋገመችው፤ ጳውሎስ ግን በዚህ እጅግ በመታወኩ ዘወር ብሎ ያን መንፈስ፣ “ከርሷ እንድትወጣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዝሃለሁ” አለው፤ መንፈሱም በዚያው ቅጽበት ወጣላት። አሳዳሪዎቿም የገንዘብ ማግኛ ተስፋቸው ወጥቶ መሄዱን በተረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጐተቱ ባለሥልጣኖች ወዳሉበት ወደ ገበያ ቦታ አመጧቸው። ገዦቹም ፊት አቅርበዋቸው እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ሳሉ፣ ከተማችንን አውከዋል፤ ደግሞም እኛ ሮማውያን መቀበል ወይም መፈጸም ያልተፈቀደልንን ልማድ በሕዝቡ መካከል ይነዛሉ።” ሕዝቡም ተባብረው በጳውሎስና በሲላስ ላይ ተነሡባቸው፤ ገዦቹም ልብሳቸው ተገፍፎ በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ። ክፉኛ ከተደበደቡ በኋላም ወደ ወህኒ ቤት አስገቧቸው፤ የወህኒ ቤት ጠባቂውም ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም ይህን የመሰለ ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፣ ወደ ወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገብቶ እግራቸውን ከግንድ ጋራ አጣብቆ አሰራቸው። እኩለ ሌሊት አካባቢ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና እየዘመሩ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ነበር፤ ሌሎቹ እስረኞችም ያዳምጧቸው ነበር። ድንገትም የወህኒ ቤቱን መሠረት የሚያናውጥ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ፤ ወዲያውም የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፈቱ፤ የሁሉም እስራት ተፈታ። የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ከእንቅልፉ ነቅቶ የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፍተው ባየ ጊዜ፣ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ። ጳውሎስ ግን ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እኛ ሁላችን እዚሁ ስላለን፣ በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርስ!” ብሎ ጮኸ። የወህኒ ቤቱ ጠባቂም መብራት ለምኖ ወደ ውስጥ ዘልሎ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ እግር ላይ ወደቀ። ይዟቸው ከወጣ በኋላ፣ “ጌቶች ሆይ፤ እድን ዘንድ ምን ላድርግ?” አላቸው። እነርሱም፣ “በጌታ በኢየሱስ እመን፤ አንተም ቤተ ሰዎችህም ትድናላችሁ” አሉት። ከዚያም ለርሱና በቤቱ ላሉት ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ተናገሩ። የወህኒ ቤት ጠባቂውም ሌሊት በዚያ ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን ዐጠበላቸው፤ ወዲያውም እርሱና ቤተ ሰቡ ሁሉ ተጠመቁ። የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ወደ ቤቱ ወስዶ ማእድ አቀረበላቸው፤ ከቤተ ሰቡም ሁሉ ጋራ በእግዚአብሔር በማመኑ በደስታ ተሞላ። ሲነጋም፣ ገዦቹ፣ “እነዚያን ሰዎች ፈተህ ልቀቃቸው” ብለው መኰንኖቻቸውን ላኩበት። የወህኒ ቤት ጠባቂውም፣ “ገዦቹ እንድትፈቱ አዝዘዋል፤ ስለዚህ ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ” ብሎ ለጳውሎስ ነገረው። ጳውሎስ ግን፣ “እኛ የሮም ዜጎች ሆነን ሳለን፣ በሕዝብ ፊት ያለ ፍርድ ደብድበው ወደ እስር ቤት ወረወሩን፤ ታዲያ አሁን በስውር ሊያስወጡን ይፈልጋሉ? ይህማ አይሆንም፤ እነርሱ ራሳቸው መጥተው ያስወጡን!” አላቸው። መኰንኖቹም ይህንኑ ቃል ለገዦቹ ነገሯቸው፤ እነርሱም ጳውሎስና ሲላስ የሮም ዜጎች መሆናቸውን ሲሰሙ ደነገጡ፤ እነርሱ ራሳቸውም መጥተው ይቅርታ ጠይቀው ከወህኒ ቤቱ አወጧቸው፤ ከተማውንም ለቅቀው እንዲሄዱ ለመኗቸው። ጳውሎስና ሲላስ ከእስር ቤቱ ከወጡ በኋላ ወደ ልድያ ቤት ሄዱ፤ በዚያም ወንድሞችን አግኝተው አበረታቷችው፤ ከዚያም በኋላ ሄዱ።
ሐዋርያት ሥራ 16 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 16
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 16:16-40
18 ቀናት
ሐዋርያው ጳውሎስ ለአንባቢዎቹ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” (የሐዋርያት ሥራ 14:22) ይላል። የሐዋርያት ሥራን ማንበብ ወይም በዓለም ዙሪያ ካሉ ክርስቲያኖችን ምስክርነት መስማት፣ የዚህን ቃል እውነት አረጋግጠዋል። አማኞች ተቃውሞ እና ስደት ይደርስባቸዋል። ምናልባት እርሶም መከራ አጋጥሞት ይሆናል። በዚህ የንባብ እቅድ ውስጥ፣ ልናበረታታዎት እና በመከራን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ማስተማር እንፈልጋለን።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች