ሐዋርያት ሥራ 16:1-10

ሐዋርያት ሥራ 16:1-10 NASV

ጳውሎስ ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራን ደረሰ። በዚያም እናቱ አይሁዳዊት ሆና በጌታ ያመነች፣ አባቱ ግን የግሪክ ሰው የሆነ፣ ጢሞቴዎስ የተባለ አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ። እርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን በነበሩት ወንድሞች ዘንድ መልካም ምስክርነት ነበረው። ጳውሎስም ይህ ሰው ከርሱ ጋራ እንዲሄድ ፈለገ፤ ስለዚህ በዚያ አካባቢ በነበሩ አይሁድ ምክንያት ይዞ ገረዘው፤ እነዚህ አይሁድ በሙሉ የጢሞቴዎስ አባት የግሪክ ሰው እንደ ሆነ ያውቁ ነበርና። እነርሱም ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው በሚያልፉበት ጊዜ፣ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም ያሳለፉትን ውሳኔ ተቀብለው እንዲጠብቁ ለምእመናኑ ይሰጡ ነበር። አብያተ ክርስቲያናትም በእምነት እየበረቱና ዕለት ዕለትም በቍጥር እየጨመሩ ይሄዱ ነበር። ጳውሎስና ባልደረቦቹ ቃሉን በእስያ እንዳይሰብኩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው፣ በፍርግያና በገላትያ አገር ዐልፈው ሄዱ። ወደ ሚስያም በተቃረቡ ጊዜ፣ ወደ ቢታንያ ሊገቡ ሞከሩ፤ ነገር ግን የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም። ስለዚህ በሚስያ በኩል አድርገው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ፣ “ወደ መቄዶንያ ተሻግረህ ርዳን” ብሎ ሲለምነው አየ። ጳውሎስ ይህን ራእይ ካየ በኋላ፣ እግዚአብሔር ወንጌልን እንድንሰብክላቸው ጠርቶናል ብለን በመወሰን ወዲያው ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ፈለግን።