ሐዋርያት ሥራ 14:11-19

ሐዋርያት ሥራ 14:11-19 NASV

ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፣ በሊቃኦንያ ቋንቋ፣ “አማልክት በሰው ተመስለው ወደ እኛ ወርደዋል!” ብለው ጮኹ፤ በርናባስን “ድያ” አሉት፤ ጳውሎስም ዋና ተናጋሪ ስለ ነበር “ሄርሜን” አሉት። ከከተማው ወጣ ብሎ የነበረው የድያ ቤተ መቅደስ ካህንም፣ ኰርማዎችንና የአበባ ጕንጕኖችን ወደ ከተማው መግቢያ አምጥቶ፣ ከሕዝቡ ጋራ ሆኖ ሊሠዋላቸው ፈለገ። ሐዋርያቱ በርናባስና ጳውሎስ ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቡ መካከል ሮጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “እናንተ ሰዎች፤ ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እኮ እንደ እናንተው ሰዎች ነን። እናንተም ደግሞ ከነዚህ ከንቱ ነገሮች ርቃችሁ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር እንድትመለሱ ወንጌልን እንሰብክላችኋለን። እርሱ ባለፉት ትውልዶች፣ ሕዝቦች ሁሉ በገዛ መንገዳቸው እንዲሄዱ ተዋቸው፤ ይሁን እንጂ ዝናብን ከሰማይ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠቱ፣ ደግሞም ልባችሁን በመብልና በደስታ በማርካቱ መልካምን በማድረግ ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” ይህን ሁሉ ተናግረው እንኳ፣ ሕዝቡ እንዳይሠዋላቸው ያስተዉት በብዙ ችግር ነበር። አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጥተው፣ ሕዝቡን አግባቡ፤ ጳውሎስንም በድንጋይ ከወገሩት በኋላ፣ የሞተ መስሏቸው ጐትተው ከከተማው ወደ ውጭ አወጡት።