ሐዋርያት ሥራ 13:26-41

ሐዋርያት ሥራ 13:26-41 NASV

“እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞች፤ ደግሞም በመካከላችሁ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፤ ይህ የድነት መልእክት የተላከው ለሁላችንም ነው። የኢየሩሳሌም ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስን አላወቁትም፤ ይሁን እንጂ በየሰንበቱ የሚነበበው የነቢያት ቃል እንዲፈጸም በርሱ ፈረዱበት። ለሞት የሚያበቃው አንድም ምክንያት ባያገኙበትም እንኳ ጲላጦስ የሞት ፍርድ እንዲፈርድበት ተማጸኑት። ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ከተሰቀለበት ዕንጨት አውርደው በመቃብር ውስጥ አስገቡት። እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው። ከገሊላ ጀምሮ እስከ ኢየሩሳሌም ከእነርሱ ጋራ ለነበሩትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን ለሕዝቡ ምስክሮቹ ናቸው። “እኛም እግዚአብሔር ለአባቶች ቃል የገባውን የምሥራች ቃል ለእናንተ እንሰብካለን፤ ኢየሱስንም ከሙታን በማስነሣቱ ለእነርሱ የገባውን ቃል ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሟል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር እንዲህ ብሎ ተጽፏል፤ “ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።’ ደግሞም፣ እርሱ እንዳልበሰበሰና እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው ለማረጋገጥ እንዲህ ብሏል፤ “ ‘የተቀደሰውንና የታመነውን፣ የዳዊትን በረከት እሰጣችኋለሁ።’ ስለዚህ በሌላም ስፍራ፣ “ ‘ቅዱስህ መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም’ ይላል። “ዳዊት በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ካገለገለ በኋላ አንቀላፍቷል፤ ከአባቶቹም ጋራ ተቀብሮ ሥጋው በስብሷል። እግዚአብሔር ከሙታን ያስነሣው እርሱ ግን መበስበስን አላየም። “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ የኀጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ በኩል መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ ሕግ በኩል ማግኘት ያልተቻለውን ጽድቅ ያገኛል። ስለዚህ ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ “ ‘እናንተ ፌዘኞች፤ ተመልከቱ፤ ተደነቁ፤ ጥፉም፤ ማንም ቢነግራችሁ እንኳን፣ የማታምኑትን ነገር፣ እኔ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’ ”