በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፣ ኔጌር የተባለው ስምዖን፣ የቀሬናው ሉክዮስ፣ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስ ዐብሮ አደግ የነበረው ምናሔ እና ሳውል ነበሩ። እነዚህም ጌታን እያመለኩና እየጾሙ ሳሉ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ “በርናባስንና ሳውልን እኔ ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አለ። እነርሱም ከጾሙና ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጭነው አሰናበቷቸው። በርናባስና ሳውልም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። ስልማና በደረሱም ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ ዮሐንስም እንደ አገልጋያቸው ዐብሯቸው ነበር። የቆጵሮስን ደሴት ከዳር እስከ ዳር አቋርጠው ጳፉ በደረሱ ጊዜ፣ በርያሱስ የተባለ አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ አገኙ፤ እርሱም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከተባለው አስተዋይ አገረ ገዥ ጋራ ነበረ። ይህ አገረ ገዥ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን አስጠራቸው። ጠንቋዩ ኤልማስ ግን፣ የስሙ ትርጕም እንዲህ ነበርና፣ አገረ ገዥው እንዳያምን ለማደናቀፍ ስለ ፈለገ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለውም ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ፣ ትኵር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፤ “አንተ የጽድቅ ሁሉ ጠላት፣ ተንኰልንና ክፋትን ሁሉ የተሞላህ የዲያብሎስ ልጅ፣ የጌታን ቀና መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም የጌታ እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውር ትሆናለህ፤ ከእንግዲህ የፀሓይን ብርሃን ለአንድ አፍታ እንኳ አታይም።” ወዲያውም ጭጋግና ጨለማ በላዩ ወረደ፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ለመፈለግ ወዲያ ወዲህ ይል ጀመር። አገረ ገዥውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ በጌታ ትምህርት በመደነቅ አመነ። ጳውሎስና ጓደኞቹ ከጳፉ ተነሥተው በጵንፍልያ ወደምትገኘው ወደ ጴርጌን ሄዱ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እነርሱ ግን ከጴርጌን ተነሥተው በጲስድያ ውስጥ ወዳለችው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ በሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ከተነበቡ በኋላ፣ የምኵራብ አለቆች፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ሕዝቡን የሚመክር ቃል ካላችሁ ተናገሩ” ሲሉ ላኩባቸው። ጳውሎስም ተነሥቶ በእጁ በመጥቀስ እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ደግሞም እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁሉ፤ አድምጡ! የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ፣ አባቶቻችንን መረጣቸው፤ በግብጽ ምድር እያሉም ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ በኀያል ክንዱም ከዚያ አወጣቸው። አርባ ዓመት ያህልም በበረሓ ታገሣቸው፤ በከነዓን ምድር የነበሩትንም ሰባት መንግሥታት አጥፍቶ፣ ምድራቸውን ለገዛ ሕዝቡ ርስት አድርጎ አወረሳቸው። ይህም ሁሉ የተፈጸመው በአራት መቶ ዐምሳ ዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ ነበር። “ከዚህ በኋላ፣ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው። ከዚያም ሕዝቡ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለመኑት፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን፣ የቂስን ልጅ ሳኦልን ሰጣቸው፤ እርሱም አርባ ዓመት ገዛቸው። ሳኦልንም ከሻረው በኋላ፣ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ እግዚአብሔርም ስለ እርሱ፣ ‘እንደ ልቤ የሆነና እኔ የምሻውን ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ሲል መሰከረለት። “እግዚአብሔርም በገባው ቃል መሠረት ከዚህ ሰው ዘር አዳኝ የሆነውን ኢየሱስን ለእስራኤል አመጣ። ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት፣ ዮሐንስ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ንስሓ ገብተው እንዲጠመቁ ሰብኮላቸው ነበር። ዮሐንስ ተልእኮውን በማጠናቀቅ ላይ ሳለ፣ ‘እኔ ማን መሰልኋችሁ? እኔ እኮ እርሱ አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግሩን ጫማ መፍታት የማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል’ ይል ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 13 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 13
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 13:1-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች