በዚያ ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባላትን እያሳደደ ያስጨንቅ ነበር፤ የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ አስገደለ። ይህ አድራጎቱ አይሁድን ደስ እንዳሰኛቸው ባየ ጊዜ፣ ጴጥሮስን ደግሞ አስያዘው፤ ይህም የሆነው በቂጣ በዓል ሰሞን ነበር። ጴጥሮስን ወህኒ ቤት ካስገባው በኋላ፣ አራት አራት ወታደሮች እየሆኑ እንዲጠብቁት በአራት ፈረቃ ለተመደቡ ወታደሮች አስረከበው፤ ይህን ያደረገውም የፋሲካ በዓል ካለፈ በኋላ ሕዝብ ፊት አውጥቶ ሊያስፈርድበት ዐስቦ ነው። ጴጥሮስም በዚህ መሠረት እስር ቤት ተጣለ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን ስለ እርሱ አጥብቃ ወደ እግዚአብሔር ትጸልይ ነበር። ሄሮድስም ጴጥሮስን ሕዝቡ ፊት ሊያቀርበው ዐስቦ ሳለ፣ ጴጥሮስ በዚያው ሌሊት በሁለት ሰንሰለት ታስሮ፣ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ የወህኒ ቤት ጠባቂዎችም እስር ቤቱ በር ላይ ቆመው ነበር። የጌታ መልአክም ድንገት ታየ፤ በክፍሉም ውስጥ ብርሃን በራ፤ መልአኩም የጴጥሮስን ጐን መታ አድርጎ ቀሰቀሰውና፣ “ቶሎ ተነሣ!” አለው፤ በዚህ ጊዜ ሰንሰለቶቹ ከእጆቹ ወደቁ። መልአኩም፣ “ልብስህን ልበስ፤ ጫማህንም አድርግ” አለው። ጴጥሮስም እንደ ታዘዘው አደረገ። መልአኩም ቀጥሎ፣ “መደረቢያህን ከላይ ጣል አድርገህ ተከተለኝ” አለው። ጴጥሮስም ተከትሎት ከእስር ቤት ወጣ፤ ነገር ግን ራእይ የሚያይ መሰለው እንጂ መልአኩ የሚያደርገው ነገር በእውን መሆኑን አላወቀም ነበር። የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ ዐልፈው ወደ ከተማዪቱ በሚወስደው መንገድ ላይ ወዳለው የብረት መዝጊያ ዘንድ ደረሱ። መዝጊያውም ራሱ ዐውቆ ተከፈተላቸው፤ እነርሱም ወጥተው ሄዱ፤ አንዲት ስላች መንገድ እንዳለፉም ወዲያው መልአኩ ተለየው። ጴጥሮስም ሲረጋጋ፣ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና አይሁድ ካሰቡብኝ ሁሉ እንዳወጣኝ አሁን ያለ ጥርጥር ዐወቅሁ” አለ። ይህን ከተረዳ በኋላም፣ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው በአንድነት ወደሚጸልዩበት፣ ማርቆስ ወደተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ። እዚያ ደርሶ የውጭውን በር ባንኳኳ ጊዜ፣ ሮዳ የተባለች አንዲት የቤት ሠራተኛ ማን እንደ ሆነ ለማጣራት ወደ በሩ ሄደች። የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ፣ በጣም ከመደሰቷ የተነሣ በሩን ሳትከፍት ሮጣ በመመለስ፣ ጴጥሮስ በሩ ላይ ቆሞ እንደሚገኝ ተናገረች። ሰዎቹም፣ “አብደሻል እንዴ!” አሏት፤ እርሷ ግን ይህንኑ ደጋግማ በነገረቻቸው ጊዜ፣ “እንግዲያውስ የርሱ መልአክ ነው” አሉ። ጴጥሮስ ግን በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ እነርሱም በሩን ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ። እርሱም ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ፣ ጌታ ከእስር ቤት እንዴት እንዳወጣው አስረዳቸው፣ “ስለ ሁኔታው ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሯቸው” አላቸው፤ ከዚያም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። በማግስቱም ጧት ወታደሮቹ፣ “ጴጥሮስ የት ገባ?” እያሉ በመካከላቸው ትልቅ ትርምስ ተፈጠረ። ሄሮድስም ጴጥሮስን አስፈልጎ ባጣው ጊዜ፣ ዘብ ጠባቂዎቹን በጥብቅ ከመረመረ በኋላ እንዲገደሉ አዘዘ። ከዚያም ሄሮድስ ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ወርዶ እዚያ ተቀመጠ። እርሱም ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎች ጋራ ጥለኛ ነበር፤ አገራቸው ምግብ የሚያገኘው ከንጉሡ ግዛት ስለ ነበር፣ የንጉሡን ባለሟል የብላስጦስን ድጋፍ ካገኙ በኋላ፣ አንድ ላይ ሆነው ከንጉሡ ጋራ ለመታረቅ ጠየቁ። በቀጠሮውም ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም ንግግር አደረገ። ሕዝቡም፣ “ይህስ የአምላክ ድምፅ እንጂ የሰው አይደለም” ብለው ጮኹ። ሄሮድስም ለእግዚአብሔር ክብር ስላልሰጠ የጌታ መልአክ ወዲያው መታው፤ በትልም ተበልቶ ሞተ። የእግዚአብሔር ቃል ግን እያደገና እየሰፋ ሄደ።
ሐዋርያት ሥራ 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 12:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች