ሐዋርያት ሥራ 10:36-43

ሐዋርያት ሥራ 10:36-43 NASV

እግዚአብሔር፣ የሁሉ ጌታ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እስራኤል ሕዝብ የላከውም የሰላም የምሥራች መልእክት ይኸው ነው። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በመላው ይሁዳ የሆነውን ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ። “እርሱ በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ላደረገው ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ ደግሞም ሰዎች እርሱን በዕንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። እግዚአብሔር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን አስነሣው፤ እንዲታይም አደረገው፤ የታየውም ለሁሉ ሰው ሳይሆን፣ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ዐብረነው ለበላንና ለጠጣን፣ እግዚአብሔርም አስቀድሞ ለመረጠን ለእኛ ለምስክሮቹ ነው። ለሕዝቡ እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታንም ላይ እንዲፈርድ እግዚአብሔር የሾመው እርሱ መሆኑን እንድንመሰክር እርሱ ራሱ አዘዘን፤ በርሱም የሚያምን ሁሉ በስሙ የኀጢአትን ስርየት እንደሚቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።”