ሐዋርያት ሥራ 10:1-33
ሐዋርያት ሥራ 10:1-33 NASV
በቂሳርያ፣ “የኢጣሊያ ክፍለ ጦር” በሚባለው ሰራዊት ውስጥ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ከመላው ቤተ ሰቡ ጋራ በመንፈሳዊ ነገር የተጋና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ለሰዎች እጅግ ምጽዋት የሚሰጥ፣ አዘውትሮ ወደ እግዚአብሔር የሚጸልይ ነበር። አንድ ቀን፣ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “ቆርኔሌዎስ ሆይ!” ሲለው በግልጽ አየ። ቆርኔሌዎስም በድንጋጤ ትኵር ብሎ እያየው፣ “ጌታ ሆይ፤ ምንድን ነው?” አለው። መልአኩም እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህና ምጽዋትህ ለመታሰቢያነት ወደ እግዚአብሔር ፊት ዐርጎልሃል። አሁንም ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣው፤ እርሱ አሁን በባሕር አጠገብ በሚገኘው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ተቀምጧል።” ቆርኔሌዎስም፣ ያነጋገረው መልአክ ተለይቶት ከሄደ በኋላ፣ ከአገልጋዮቹ ሁለቱን፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ነገር የተጋና ለርሱ ታማኝ የሆነውን አንዱን ወታደር አስጠራ፤ የሆነውንም ነገር ሁሉ ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው። የተላኩትም ሰዎች በማግስቱም ወደ ከተማዪቱ እንደ ተቃረቡ፣ ጴጥሮስ እኩለ ቀን ገደማ ሲሆን፣ ለመጸለይ ወደ ሰገነት ወጣ። በዚያ ጊዜም ስለ ተራበ የሚበላ ነገር ፈለገ፤ ምግብ እየተዘጋጀ ሳለም አሸለበውና በተመስጦ ውስጥ ሆነ፤ ሰማይም ተከፍቶ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራት ማእዘን ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድ አየ። በጨርቁም ላይ አራት እግር ያላቸው የተለያዩ እንስሳት፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትና በአየር የሚበርሩ አዕዋፍ ነበሩበት። በዚህ ጊዜ፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣ፤ እነዚህን ዐርደህ ብላ” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! ይህማ አይሆንም፤ እኔ ያልተቀደሰ ወይም ርኩስ ነገር ፈጽሞ በልቼ አላውቅምና” አለ። ያም ድምፅ እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኩስ አትቍጠረው” አለው። ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ጨርቁም ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስም ስላየው ራእይ ትርጕም እጅግ ተጨንቆ በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች የስምዖንን ቤት ፈልገው ካገኙ በኋላ መጥተው በሩ ላይ ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን እዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ። ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ መንፈስ እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ስለዚህ ተነሥተህ ውረድ፤ የላክኋቸውም እኔ ስለ ሆንሁ፣ ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋራ ሂድ።” ጴጥሮስም ወርዶ፣ “እነሆ፤ የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበት ጕዳይ ምንድን ነው?” አላቸው። ሰዎቹ፣ “የመጣነው ቆርኔሌዎስ ከተባለው መቶ አለቃ ዘንድ ነው፤ እርሱም ጻድቅና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተከበረ ሰው ነው። አንተን ወደ ቤቱ እንዲያስመጣህና የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ነግሮታል” አሉት። ጴጥሮስም ሰዎቹን ሊያስተናግዳቸው ወደ ቤት አስገባቸው። ጴጥሮስም በማግስቱም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋራ ሄደ፤ ከኢዮጴ የመጡ አንዳንድ ወንድሞችም ዐብረውት ሄዱ፤ በሚቀጥለው ቀን ቂሳርያ ገባ። ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ ይጠብቃቸው ነበር። ጴጥሮስም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ እግሩም ላይ ወድቆ ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን፣ “እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝና ተነሥ!” ብሎ አስነሣው። ጴጥሮስም እያነጋገረው ዐብሮት ሲገባ፣ ብዙ ሰው ተሰብስቦ አገኘ፤ እንዲህም አላቸው፤ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ወገን ጋራ እንዲተባበር ወይም እንዲቀራረብ ሕጋችን እንደማይፈቅድ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እኔ ማንንም ርኩስ ወይም ያልተቀደሰ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳይቶኛል። ስለዚህም በተጠራሁ ጊዜ፣ እነሆ ሳላመነታ መጣሁ፤ እንግዲህ፣ ለምን እንደ ጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።” ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፤ “ከአራት ቀን በፊት በዚህ ጊዜ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ ሆኜ እጸልይ ነበር፤ ድንገትም ብሩህ ልብስ የለበሰ ሰው መጥቶ በፊቴ ቆመና እንዲህ አለኝ፤ ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ፤ ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ምጽዋትህም ለመታሰቢያነት በእግዚአብሔር ፊት ደርሷል። ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣው፤ እርሱም በባሕሩ አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ዐርፏል።’ እኔም ወዲያው ላክሁብህ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ እኛ ሁላችን ጌታ ያዘዘህን ስትነግረን ለመስማት በእግዚአብሔር ፊት አለን።”

