2 ሳሙኤል 7:18-29

2 ሳሙኤል 7:18-29 NASV

ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ በፊትህ ጥቂት ሆኖ ሳለ አንተ ግን ስለ ወደ ፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ፤ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰው ጋራ የምታደርገው ግንኙነት ለካ እንዲህ ነው? “ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህን አንተ ታውቀዋለህ፤ ስለ ቃልህና እንደ ልብህ ሐሳብ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ ባሪያህም እንዲያውቀው ገልጸህለታል። “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት ታላቅ ነህ! እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ በጆሯችን እንደ ሰማነው ሁሉ፣ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። “ለራሱ ሕዝብ ይሆን ዘንድ ሊታደገው፣ እግዚአብሔር በፊቱ እንደሄደለት ሕዝብ፣ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ አሕዛብንና አማልክታቸውን ከፊቱ አሳድዶ ታላላቅና አስፈሪ ታምራት እንዳደረገለትና ከግብጽም እንደ ተቤዠው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ማን አለ? ሕዝብህን እስራኤልን ለዘላለም የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆነኸዋል። “አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህና ለቤቱ የሰጠኸውን ተስፋ ለዘላለም የጸና ይሁን፤ እንደተናገርኸውም ፈጽም፤ ስለዚህ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሆናል፤ ሰዎችም፣ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይላሉ። የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል። “አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ‘እኔ ለአንተ ቤት እሠራልሃለሁ’ ብለህ ይህን ለባሪያህ ገልጸህለታል። ስለዚህ ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ በልቡ ደፈረ። አሁንም ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህም የታመነ ነው፤ ይህንም መልካም ነገር ለማድረግ ለባሪያህ ተስፋ ሰጥተኸዋል፤ በፊትህ ለዘላለም ጸንቶ እንዲኖር፣ አሁንም የባሪያህን ቤት እባክህ ባርክ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አንተው ራስህ ተናግረሃል፤ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘላለም ይባረካል።”