2 ሳሙኤል 5:1-25

2 ሳሙኤል 5:1-25 NASV

የእስራኤል ነገዶች በሙሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ እኛ የዐጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤ በቀደመው ዘመን ሳኦል በእኛ ላይ ንጉሥ በነበረ ጊዜ፣ እስራኤልን በጦርነት የምትመራ አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፤ መሪያቸውም ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።” ስለዚህ የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ንጉሥ ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን አደረገ፤ እነርሱም ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት። ዳዊት በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ፤ አርባ ዓመትም ገዛ። በኬብሮን ተቀምጦ በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር፣ ኢየሩሳሌም ሆኖም በመላው እስራኤልና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ። ንጉሡና ሰዎቹ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ለመውጋት ወደዚያ ሄዱ። ኢያቡሳውያንም፣ “ዳዊት እዚህ ሊገባ አይችልም” ብለው ስላሰቡ ዳዊትን፣ “ዕውሮችና ዐንካሶች እንኳ ይከለክሉሃልና ወደዚህች አትገባም” አሉት። ይሁን እንጂ ዳዊት የጽዮንን ዐምባ ያዘ፤ ይህችም የዳዊት ከተማ የተባለችው ናት። በዚያም ዕለት ዳዊት፣ “ኢያቡሳውያንን ድል ማድረግ የሚፈልግ፣ የዳዊት ጠላቶች ወደሚሆኑ፣ ‘ዐንካሶችና ዕውሮች’ ለመድረስ በውሃ መተላለፊያው ሽቅብ መውጣት አለበት” አለ። እንግዲህ፣ “ ‘ዐንካሶችና ዕውሮች’ ወደ ቤተ መንግሥት አይገቡም” ያሉት ለዚህ ነው። ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በዐምባዪቱ ላይ አደረገ፤ የዳዊት ከተማም ብሎ ጠራት። ዳዊትም ከሚሎ አንሥቶ ወደ ውስጥ ዙሪያዋን ገነባት። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበር፣ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ። በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ እንዲሁም የዝግባ ዕንጨት፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ድንጋይ ጠራቢዎችን ዐብሮ ሰደደ፤ እነርሱም ለዳዊት ቤተ መንግሥት ሠሩለት። ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፣ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም ሲል መንግሥቱን ከፍ ከፍ እንዳደረገለት ተገነዘበ። ዳዊት ከኬብሮን ከሄደ በኋላ፣ በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ሚስቶች አገባ፤ ቁባቶችንም አስቀመጠ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት። በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣ ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ናፌቅ፣ ያፍያ፣ ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት ይባላሉ። ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ፍለጋ በሙሉ ኀይላቸው ወጡ፤ ዳዊትም ይህን ሰምቶ ወደ ምሽጉ ወረደ። በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ። ስለዚህም ዳዊት፣ “በፍልስጥኤማውያን ላይ ወጥቼ ልምታቸውን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን ሂድ፤ በርግጥ ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው። ስለዚህም ዳዊት ወደ በኣልፐራሲም ሄዶ ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው። እርሱም “የጐርፍ ውሃ ጥሶ በመውጣት እንደሚያፈራርስ፣ እግዚአብሔርም ጠላቶቼን በፊቴ አፈራረሳቸው” አለ። ከዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም “በኣልፐራሲም” ተባለ። ፍልስጥኤማውያንም ጣዖቶቻቸውን ትተው ሸሽተው ስለ ነበር፣ ዳዊትና ሰዎቹ ወስደው አቃጠሏቸው። ፍልስጥኤማውያን እንደ ገና መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ። ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በስተ ኋላቸው በኩል በመክበብ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ በቀጥታ ወዳሉበት አትውጣ፤ በሾላ ዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ጕዞ ድምፅ ስትሰማም፣ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመምታት ቀድሞህ ወጥቷል ማለት ነውና በዚያ ጊዜ በፍጥነት ወደ ፊት ሂድ።” ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ከገባዖን እስከ ጌዝር ድረስ እያሳደደ መታቸው።