2 ሳሙኤል 24:4-15

2 ሳሙኤል 24:4-15 NASV

ሆኖም የንጉሡ ቃል ኢዮአብንና የሰራዊቱን አዛዦች ስላሸነፋቸው፣ የእስራኤልን ሰራዊት ለመመዝገብ ከፊቱ ወጥተው ሄዱ። ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ፣ በሸለቆው ውስጥ ካለችው ከተማ በስተ ደቡብ በምትገኘው በአሮዔር አጠገብ ሰፈሩ፤ ከዚያም በጋድ በኩል አድርገው ወደ ኢያዜር ሄዱ፤ እንዲሁም ወደ ገለዓድና ወደ ተባሶን አዳሰይ፣ ቀጥሎም ወደ ዳንየዓን ከዚያም ዞረው ወደ ሲዶና ሄዱ። ደግሞም ወደ ጢሮስ ምሽግ፣ ወደ ኤዊያውያንና ወደ ከነዓናውያን ከተሞች፣ በመጨረሻም በይሁዳ ደቡብ ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ። ምድሪቱን ሁሉ ዞረው ከዘጠኝ ወር ከሃያ ቀን በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ኢዮአብም የተዋጊዎቹን ጠቅላላ ቍጥር ለንጉሡ አሳወቀ፤ በእስራኤል ስምንት መቶ ሺሕ፣ በይሁዳ ዐምስት መቶ ሺሕ ሰይፍ መምዘዝ የሚችሉ ብቃት ያላቸው ሰዎች ተገኙ። ዳዊት ተዋጊዎቹን ከቈጠረ በኋላ ኅሊናው ስለ ወቀሠው፣ “ባደረግሁት ነገር ታላቅ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ የአገልጋይህን በደል እንድታርቅ እለምንሃለሁ፤ የፈጸምሁት ታላቅ የስንፍና ሥራ ነውና” አለ። በማግስቱም ጧት ዳዊት ከመነሣቱ በፊት የእግዚአብሔር ቃል የዳዊት ባለራእይ ወደ ሆነው ወደ ነቢዩ ወደ ጋድ መጣ፤ እንዲህም አለው፤ “ሂድና ዳዊትን፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሦስት ነገሮችን ለምርጫ አቅርቤልሃለሁ፤ በአንተ ላይ አደርግብህ ዘንድ አንዱን ምረጥ’ በለው።” ስለዚህም ጋድ ወደ ዳዊት ሄዶ፣ “በምድርህ የሦስት ዓመት ራብ ይምጣብህ? ወይስ ጠላቶችህ እያሳደዱህ ሦስት ወር ትሸሽ? ወይስ ደግሞ በምድርህ ላይ የሦስት ቀን መቅሠፍት ይምጣ? እንግዲህ አሁን ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ ዐስበህበት ወስን” አለው። ዳዊትም ጋድን፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ታላቅ ስለ ሆነ በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፤ በሰው እጅስ አልውደቅ” አለ። ስለዚህም እግዚአብሔር ከዚያች ዕለት ጧት አንሥቶ እስከ ተወሰነው ቀን ድረስ በእስራኤል ላይ መቅሠፍት ላከ፤ በዚህም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሰባ ሺሕ ሰው ዐለቀ።