2 ሳሙኤል 19:1-23

2 ሳሙኤል 19:1-23 NASV

ለኢዮአብ፣ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰ እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው። ንጉሡ፣ “ስለ ልጁ ዐዝኗል” መባሉን በዚያ ቀን ሰራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሰራዊት ዘንድ ወደ ሐዘን ተለውጦ ዋለ። በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ተሸማቆ ወደ ከተማ ገባ። ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፤ ልጄን! ወየው ልጄን!” እያለ ጮኸ። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፣ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፣ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍረሃቸዋል። የሚጠሉህን ትወድዳለህ፤ የሚወድዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳይደሉ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን ዐልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ። በል አሁን ተነሥተህ ውጣና ሰዎችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው ዐብሮህ እንደማይሆን በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያስከትልብሃል።” ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በበሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም፣ “እነሆ ንጉሡ በበሩ አጠገብ ተቀምጧል” ተብሎ በተነገረ ጊዜ ሕዝቡ በሙሉ ወደ ንጉሡ መጣ። በዚያ ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ ወደ የቤታቸው ሸሽተው ነበር። በመላው የእስራኤል ነገዶችም፣ ሕዝቡ እንዲህ እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር፤ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ የታደገን እርሱ ነው፤ አሁን ግን በአቤሴሎም ምክንያት ከአገር ሸሽቶ ሄዷል፤ በላያችን ሆኖ እንዲገዛን የቀባነው አቤሴሎም ደግሞ በጦርነት ሞቷል፤ ታዲያ ንጉሡን የመመለሱን ጕዳይ ለምንድን ነው ዝም የምትሉት?” ንጉሥ ዳዊት ወደ ካህናቱ ወደ ሳዶቅና ወደ አብያታር እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የይሁዳ ሽማግሌዎችን እንዲህ በሏቸው አለ፤ ‘በመላው እስራኤል የሚባለው ሁሉ ለንጉሡ ባለበት የደረሰው ስለ ሆነ፣ ንጉሡን ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ? እናንተ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ ወንድሞቼ ናችሁ፤ ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ?’ አሜሳይንም፣ ‘አንተስ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ አይደለህምን? ከአሁን ጀምሮ እስከ ሕይወትህ ፍጻሜ በኢዮአብ ምትክ የሰራዊቴ አዛዥ ባላደርግህ፣ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፣ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ’ ብላችሁ ንገሩት።” እርሱም የይሁዳን ሰዎች ልብ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ ማረከው፤ እነርሱም “አንተም ሰዎችህም ሁሉ ተመለሱ” ብለው ወደ ንጉሡ ላኩበት። ከዚያም ንጉሡ ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን ተቀብለው ዮርዳኖስን ለማሻገር እስከ ጌልገላ ድረስ መጥተው ነበር። የባሑሪም ሰው የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሳሚ ከይሁዳ ሰዎች ጋራ ሆኖ ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ፈጥኖ ወረደ። ከርሱም ጋራ አንድ ሺሕ ብንያማውያን፣ እንዲሁም የሳኦል ቤተ ሰብ አገልጋይ ሲባ ከዐሥራ ዐምስት ወንዶች ልጆቹና ከሃያ አሽከሮቹ ጋራ ሆኖ ዐብረውት ነበሩ። ከዚያም ንጉሡ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ በጥድፊያ ወረዱ። የንጉሡን ቤተ ሰው ለማምጣትና እርሱ የሚፈልገውንም ሁሉ ለማድረግ በመልካው ተሻገሩ። የጌራ ልጅ ሳሚ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ በንጉሡም ፊት ተደፍቶ፣ እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ በደሌን አይቍጠርብኝ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከኢየሩሳሌም በወጣህባት ዕለት የፈጸምሁትን ስሕተት እርሳው፤ ከአእምሮህም አውጣው። እኔ አገልጋይህ ኀጢአት መሥራቴን ዐውቃለሁና፤ ዛሬ ግን ጌታዬን ንጉሡን ለመቀበል ከዮሴፍ ቤት ሁሉ የመጀመሪያ ሆኜ እነሆ መጥቻለሁ።” ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ፣ “ሳሚ በእግዚአብሔር የተቀባውን የረገመ ስለ ሆነ፣ መሞት አይገባውምን?” አለ። ዳዊትም፣ “እናንተ የጽሩያ ልጆች፣ እናንተንና እኔን ምን የሚያገናኘን ነገር አለ? ዛሬ ጠላት ሆናችሁኛል! ማንስ ቢሆን ዛሬ በእስራኤል ዘንድ ሰው መሞት አለበት? እኔ በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁበት ቀን አይደለምን?” ብሎ መለሰ። ስለዚህ ንጉሡ ሳሚን፣ “አትሞትም” አለው፤ ይህንም ንጉሡ በመሐላ አጸናለት።