2 ጴጥሮስ 3:10-18

2 ጴጥሮስ 3:10-18 NASV

የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ፍጥረትም በታላቅ ግለት ይጠፋል፤ ምድርና በርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ወና ይሆናል። እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል። በዚያ ቀን ሰማያት በእሳት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በታላቅ ትኵሳት ይቀልጣል። እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን። ስለዚህ ወዳጆች ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የምትጠባበቁ ስለ ሆናችሁ፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከርሱ ጋራ በሰላም እንድትገኙ ትጉ። የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደ ሆነ አስቡ፤ እንዲሁም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ። እርሱ ስለ እነዚህ ነገሮች በመልእክቶቹ ሁሉ ጽፏል፤ በመልእክቶቹም ውስጥ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግቱ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ፣ እነዚህንም ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ። እንግዲህ ወዳጆች ሆይ፤ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ፣ ጸንታችሁ ከቆማችሁበት መሠረት በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ። ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ።