2 ጴጥሮስ 1:5-15

2 ጴጥሮስ 1:5-15 NASV

በዚህም ምክንያት በሙሉ ትጋት በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ለመጨመር ጣሩ፤ በበጎነት ላይ ዕውቀትን፣ በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፣ በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ባሕርያት ተትረፍርፈው ቢኖሯችሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ዳተኞችና ፍሬ ቢሶች ከመሆን ይጠብቋችኋል። እነዚህ ባሕርያት የሌሉት ግን የሩቁን የማያይ ወይም ዕውር ነው፤ ከቀድሞው ኀጢአቱ መንጻቱንም ረስቷል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ለማጽናት ከፊት ይልቅ ትጉ፤ ምክንያቱም እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም። በዚህም ወደ ጌታችንና አዳኛችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋል። ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች ብታውቋቸውና በያዛችሁት እውነት ብትጸኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች እናንተን ዘወትር ከማሳሰብ ቸል አልልም። በዚህ ምድራዊ ድንኳን ውስጥ እስካለሁ ድረስ እናንተን መጐትጐት ትክክል ሆኖ ይታየኛል፤ ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ገለጠልኝ ይህን ምድራዊ ድንኳን ቶሎ ጥዬ እንደምሄድ ዐውቃለሁ፤ እነዚህን ነገሮች ከተለየኋችሁም በኋላ ዘወትር ታስቡ ዘንድ እተጋለሁ።