2 ጴጥሮስ 1:12-21

2 ጴጥሮስ 1:12-21 NASV

ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች ብታውቋቸውና በያዛችሁት እውነት ብትጸኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች እናንተን ዘወትር ከማሳሰብ ቸል አልልም። በዚህ ምድራዊ ድንኳን ውስጥ እስካለሁ ድረስ እናንተን መጐትጐት ትክክል ሆኖ ይታየኛል፤ ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ገለጠልኝ ይህን ምድራዊ ድንኳን ቶሎ ጥዬ እንደምሄድ ዐውቃለሁ፤ እነዚህን ነገሮች ከተለየኋችሁም በኋላ ዘወትር ታስቡ ዘንድ እተጋለሁ። ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀይልና ስለ መምጣቱ የነገርናችሁ የርሱን ግርማ በዐይናችን አይተን እንጂ፣ በሰዎች ጥበብ የተፈጠረውን ተረት ተከትለን አይደለም፤ ምክንያቱም ከግርማዊው ክብር “በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርና ሞገስ ተቀብሏል፤ እኛም ከርሱ ጋራ በቅዱሱ ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ ይህ ድምፅ ከሰማይ ሲመጣ ሰምተናል። እንግዲያስ ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪበራ ድረስ፣ በጨለማ ስፍራ ለሚበራ መብራት ጥንቃቄ እንደሚደረግ እናንተም ለዚህ ቃል ብትጠነቀቁ መልካም ታደርጋላችሁ። ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ልታውቁ ይገባችኋል፤ በመጽሐፍ ያለው የትንቢት ቃል ሁሉ ማንም ሰው በገዛ ራሱ መንገድ የሚተረጕመው አይደለም፤ ምክንያቱም ትንቢት ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የተናገሩት እንጂ ከቶ በሰው ፈቃድ የመጣ አይደለም።