2 ነገሥት 8:16-24

2 ነገሥት 8:16-24 NASV

የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐምስተኛው ዓመት፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ይሆራም በይሁዳ ነገሠ። እርሱ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ። እርሱም የአክዓብን ልጅ አግብቶ ስለ ነበር፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም የእስራኤል ነገሥታት የሄዱበትን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። ይሁን እንጂ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት ሲል፣ እግዚአብሔር ይሁዳን ማጥፋት አልፈለገም፤ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም መብራት እንደሚሰጥ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና። በይሆራም ዘመነ መንግሥት፣ ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐምፆ የራሱን ንጉሥ አነገሠ። ስለዚህም ኢዮራም ሠረገሎቹን ሁሉ አሰልፎ ወደ ጸዒር ተሻገረ። በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሠረገላ አዛዦቹን ሁሉ የከበቧቸውን ኤዶማውያንን መታ፤ ሰራዊቱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። ኤዶም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንዳመፀ ነው፤ ልብናም በዚሁ ጊዜ ዐምፆ ነበር። በኢዮራም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? ኢዮራምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እንደ እነርሱም ሁሉ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አካዝያስም በምትኩ ነገሠ።