በዚህ ጊዜ የሚያሠቅቅ የቈዳ በሽታ የያዛቸው አራት ሰዎች በከተማዪቱ መግቢያ በር አጠገብ ነበሩ፤ እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “እስክንሞት ድረስ በዚህ የምንቈየው ለምንድን ነው? ታዲያ፣ ‘ወደ ከተማዪቱ እንግባ ብንል’ በዚያም ራብ ስላለ እንሞታለን፤ በዚሁም ብንሆን ያው መሞታችን አይቀርም፤ ስለዚህ ወደ ሶርያውያኑ ሰፈር ዝም ብለን እንሂድ፤ ዝም ካሉን ሕይወታችን ትተርፋለች፤ ከገደሉንም ሞቶ መገላገል ነው።” ከዚያም መሸትሸት ሲል ተነሥተው ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄዱ፤ ወደ ሰፈሩ ጥግ ሲደርሱም አንድም ሰው በዚያ አልነበረም። ይህ የሆነበትም ምክንያት፣ እግዚአብሔር የሠረገሎችንና የፈረሶችን እንዲሁም የብዙ ሰራዊት ድምፅ ሶርያውያን እንዲሰሙ አድርጎ ስለ ነበር ነው፤ እርስ በርሳቸውም፣ “እነሆ፣ የእስራኤል ንጉሥ በእኛ ላይ አደጋ ለመጣል፣ የኬጢያውያንንና የግብጻውያንን ነገሥታት ቀጥሮ አምጥቶብናል” ተባባሉ። ከዚያም መሸትሸት ሲል ተነሥተው ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውን፣ ፈረሶቻቸውንና አህዮቻቸውንም አልወሰዱም ነፍሳቸውን ብቻ ለማዳን ሲሉ ሰፈሩን እንዲሁ እንዳለ ትተው ሄዱ። ለምጽ ያለባቸውም ሰዎች ወደ ሰፈሩ አጠገብ ከደረሱ በኋላ፣ ከድንኳኖቹ ወደ አንዱ ገብተው በሉ፤ ጠጡም፤ ከዚያም ብር፣ ወርቅና ልብስ ይዘው በመሄድ ደበቁት። ተመልሰው በመምጣትም ወደ ሌላው ድንኳን ገብተው ሌሎች ነገሮችን በመውሰድ እንደዚሁ ደበቁ። እርስ በርሳቸውም፣ “ያደረግነው ትክክል አይደለም፤ ዕለቱ የምሥራች ቀን ነው፤ እኛ ግን የራሳችን ብቻ አደረግነው፤ እስኪነጋም ከቈየን በደለኞች እንሆናለን፤ ስለዚህ ወደ ቤተ መንግሥት በፍጥነት ሄደን እንንገር” ተባባሉ። ስለዚህ ሄደው የከተማዪቱን መግቢያ በር ጠባቂዎች ጮኸው በመጥራት፣ “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ገባን፤ እዚያም ከታሰሩ ፈረሶችና አህዮች በቀር አንድም ሰው አልነበረም፤ የማንም ድምፅ አልተሰማም፤ ድንኳኖቹም እንዳሉ ናቸው” ብለው ነገሯቸው። የበሩ ጠባቂዎችም ይህንኑ አስተጋቡ፤ ዜናውም በቤተ መንግሥቱ ተሰማ። ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ለጦር አለቆቹ እንዲህ አላቸው፤ “ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ መራባችንን ስለሚያውቁ፣ ‘መቼም መውጣታቸው አይቀርም፤ ከዚያም ከነሕይወታቸው እንማርካቸዋለን፤ እኛም ሰተት ብለን ወደ ከተማዪቱ እንገባለን’ በማለት በገጠር ለመደበቅ ከሰፈራቸው ወጥተዋል።” ከጦር አለቆቹም አንዱ እንዲህ አለ፤ “ጥቂት ሰዎች በከተማዪቱ ውስጥ ከተረፉት ፈረሶች ዐምስቱን ይዘው ይሂዱ፤ ዕጣ ፈንታቸውም በዚህ ከቀሩት እስራኤላውያን ሁሉ ዕድል ጋራ አንድ ነው፤ የሚጠብቃቸው ቢኖር በዚህ በሙሉ እንዳለቁት እስራኤላውያን መሆን ብቻ ነው፤ ስለዚህ እንላካቸውና የሆነውን እንይ።” ስለዚህ ሁለት ሠረገሎች ከነፈረሶቻቸው መረጡ፤ ንጉሡም፣ “ሂዱና የሆነውን ነገር እዩ” ብሎ ከሶርያውያን ሰራዊት በኋላ እንዲሄዱ ላካቸው። እነርሱም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ተከተሏቸው። ሶርያውያን በጥድፊያ ሲሸሹ፣ የጣሉትንም ልብስና ዕቃ በየመንገዱ ላይ ተበታትኖ አገኙ፤ መልእክተኞቹም ተመልሰው ይህንኑ ለንጉሡ ነገሩት። ከዚያም ሕዝቡ ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው አንድ መስፈሪያ ማለፊያ ዱቄት በአንድ ሰቅል፣ ሁለት መስፈሪያ ገብስም በአንድ ሰቅል ተሸጠ።
2 ነገሥት 7 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ነገሥት 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ነገሥት 7:3-16
5 ቀናት
በእምነት ለመቆም፣ በእምነት የተሞሉ ፀሎቶችን ለመጸለይ እና በሕይወትዎና በሌሎችም ሕይወት ውስጥ ለመንግሥቱ አስገራሚ ነገሮችን ለማከናወን እግዚአብሔር ሊጠቀምብዎት ይችላል። የሚቅጥሉትን 5 ቀናት ይህን እምነቶን በማሳደግ ያሳልፉ።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች